ምሳሌ 26:1-28
26 በረዶ በበጋ፣ ዝናብም በመከር እንደማያስፈልግ ሁሉክብርም ለሞኝ ሰው አይገባውም።+
2 ወፍ ቱር የምትልበት፣ ወንጭፊትም የምትበርበት ምክንያት እንዳላት ሁሉእርግማንም ያለበቂ ምክንያት አይመጣም።*
3 አለንጋ ለፈረስ፣ ልጓም ለአህያ፣+በትርም ለሞኞች ጀርባ ነው።+
4 ለሞኝ እንደ ሞኝነቱ አትመልስለት፤አለዚያ አንተም የእሱ ቢጤ ትሆናለህ።*
5 ጥበበኛ የሆነ እንዳይመስለውለሞኝ እንደ ሞኝነቱ መልስለት።+
6 አንድን ጉዳይ ለሞኝ በአደራ የሚሰጥእግሩን ከሚያሽመደምድና ራሱን ከሚጎዳ* ሰው ተለይቶ አይታይም።
7 በሞኞች አፍ የሚነገር ምሳሌ፣እንደ አንካሳ ሰው እግር* ነው።+
8 ለሞኝ ክብር መስጠት፣በወንጭፍ ላይ ድንጋይ እንደ ማሰር ነው።+
9 በሞኞች አፍ የሚነገር ምሳሌበሰካራም እጅ እንዳለ እሾህ ነው።
10 ሞኝን ወይም አላፊ አግዳሚውን የሚቀጥር፣በነሲብ ያገኘውን ሁሉ* እንደሚያቆስል ቀስተኛ ነው።
11 ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ፣ሞኝ ሰውም ሞኝነቱን ይደጋግማል።+
12 ጥበበኛ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው አይተህ ታውቃለህ?+
ከእሱ ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው።
13 ሰነፍ “በመንገድ ላይ ደቦል አንበሳ፣በአደባባይም አንበሳ አለ!” ይላል።+
14 በር በማጠፊያው* ላይ እንደሚዞር፣ሰነፍም በአልጋው ላይ ይገላበጣል።+
15 ሰነፍ እጁን ወደ ሳህን ያጠልቃል፤ወደ አፉ ለመመለስ ግን እጅግ ይታክታል።+
16 ሰነፍ ሰው በማስተዋል መልስ ከሚሰጡ ሰባት ሰዎች ይበልጥጥበበኛ የሆነ ይመስለዋል።
17 በሌሎች ጠብ የሚቆጣ* መንገደኛየውሻ ጆሮ እንደሚይዝ ሰው ነው።+
18 የሚንበለበሉ ተወንጫፊ መሣሪያዎችን፣ ፍላጻዎችንና ሞትን* እንደሚወረውር እብድ፣
19 ባልንጀራውን አታሎ ሲያበቃ “ቀልዴን እኮ ነው!” የሚል ሰውም እንዲሁ ነው።+
20 እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ስም አጥፊ ከሌለ ደግሞ ጭቅጭቅ ይበርዳል።+
21 ከሰል ፍምን፣ እንጨትም እሳትን እንደሚያቀጣጥልጨቅጫቃ ሰውም ጠብ ይጭራል።+
22 ስም አጥፊ የሚናገረው ቃል ጣፋጭ እንደሆነ ቁራሽ ምግብ ነው፤*በፍጥነት ተውጦ በቀጥታ ወደ ሆድ ይገባል።+
23 ከክፉ ልብ የሚወጡ የፍቅር ቃላት፣*በቀለጠ ብር እንደተለበጠ የሸክላ ዕቃ ስባሪ ናቸው።+
24 ሌሎችን የሚጠላ ሰው ጥላቻውን በከንፈሩ ይደብቃል፤በውስጡ ግን ተንኮል ይቋጥራል።
25 አነጋገሩን ቢያሳምርም እንኳ አትመነው፤በልቡ ውስጥ ሰባት አስጸያፊ ነገሮች አሉና።*
26 ጥላቻው በተንኮል ቢሸፈንምክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል።
27 ጉድጓድ የሚቆፍር እሱ ራሱ እዚያ ውስጥ ይወድቃል፤ድንጋይ የሚያንከባልልም ወደ እሱ ተመልሶ ይመጣበታል።+
28 ውሸታም ምላስ የጎዳቻቸውን ሰዎች ትጠላለች፤የሚሸነግል አንደበትም ጥፋት ያስከትላል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ተገቢ ያልሆነ እርግማንም በሰው ላይ አይደርስም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “አለዚያ አንተም እኩያው ትሆናለህ።”
^ ቃል በቃል “ዓመፅን ከሚጋት።”
^ ወይም “እንደ ሽባ ሰው የተንጠለጠለ እግር።”
^ ወይም “ሰውን ሁሉ።”
^ ወይም “በመሽከርከሪያው።”
^ “ጣልቃ የሚገባ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ገዳይ ፍላጻዎችን።”
^ ወይም “ተስገብግበው እንደሚውጡት ነገር ነው።”
^ ቃል በቃል “ኃይለኛ ስሜትን የሚገልጽ ከንፈር።”
^ ወይም “ልቡ ሙሉ በሙሉ አስጸያፊ ነውና።”