ኢዮብ 9:1-35

  • ኢዮብ የሰጠው መልስ (1-35)

    • ሟች ሰው ከአምላክ ጋር ሊሟገት አይችልም (2-4)

    • ‘‘አምላክ የማይመረመሩ ነገሮችን ያደርጋል’ (10)

    • ሰው ከአምላክ ጋር ሊከራከር አይችልም (32)

9  ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦  2  “እርግጥ ነገሩ እንዲህ መሆኑን አውቃለሁ። ሆኖም ሟች የሆነ ሰው ከአምላክ ጋር ተሟግቶ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል?+  3  ሰው ከእሱ ጋር መሟገት ቢፈልግ፣*+አምላክ ከሚያቀርብለት አንድ ሺህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱ እንኳ መልስ መስጠት አይችልም።  4  እሱ ጥበበኛ ልብ አለው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው።+ እሱን ተገዳድሮ ከጉዳት ማምለጥ የሚችል ማን ነው?+  5  ማንም ሳያውቅ ተራሮችን ከስፍራቸው ይወስዳል፤*በቁጣውም ይገለብጣቸዋል።  6  ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፤በመሆኑም ምሰሶዎቿ ይንቀጠቀጣሉ።+  7  ብርሃን እንዳትፈነጥቅ ፀሐይን ያዛታል፤የከዋክብትን ብርሃን ያሽጋል፤+  8  ሰማያትንም ብቻውን ይዘረጋል፤+ከፍ ባለው የባሕር ማዕበልም ላይ ይራመዳል።+  9  የአሽ፣* የከሲልና* የኪማ ኅብረ ከዋክብትን*+እንዲሁም የደቡቡን ሰማይ ኅብረ ከዋክብት* ሠርቷል፤ 10  ታላላቅና የማይመረመሩ ነገሮችን፣ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ድንቅ ነገሮች ያደርጋል።+ 11  በአጠገቤ ያልፋል፤ እኔ ግን ላየው አልችልም፤አልፎኝ ይሄዳል፤ እኔ ግን አለየውም። 12  አንዳች ነገር ነጥቆ ሲወስድ ማን ሊከለክለው ይችላል? ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ሊለው የሚችልስ ማን ነው?+ 13  አምላክ ቁጣውን አይገታም፤+የረዓብ*+ ረዳቶች እንኳ እግሩ ሥር ይወድቃሉ። 14  በመሆኑም ለእሱ መልስ ስሰጥ፣ይልቁንም ከእሱ ጋር ስከራከር አስቤ መናገር ይጠበቅብኛል። 15  ትክክል ብሆን እንኳ መልስ አልሰጠውም።+ ዳኛዬን* ምሕረት ከመለመን ሌላ ምንም ማድረግ አልችልም። 16  ብጠራው ይመልስልኛል? እኔ እንደሆነ፣ ስናገር ይሰማኛል የሚል እምነት የለኝም፤ 17  በአውሎ ነፋስ ያደቀኛልና፤ያለምክንያትም ቁስሌን ያበዛል።+ 18  ለመተንፈስ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤መራራ ነገሮችን ያጠግበኛል። 19  የኃይል ጉዳይ ከሆነ እሱ ኃያል ነው።+ የፍትሕ ጉዳይ ከተነሳ ‘ማን ሊጠይቀኝ* ይችላል?’ ይላል። 20  ትክክል ብሆን እንኳ የገዛ አፌ ይፈርድብኛል፤ንጹሕ አቋሜን ብጠብቅ እንኳ* እሱ ጥፋተኛ* ነህ ይለኛል። 21  ንጹሕ አቋሜን ብጠብቅ እንኳ* ስለ ራሴ እርግጠኛ አይደለሁም፤*ይህን ሕይወቴን እጠላዋለሁ።* 22  ምንም ለውጥ የለውም። ‘እሱ ንጹሑንም* ሆነ ክፉውን ያጠፋል’የምለው ለዚህ ነው። 23  ደራሽ ውኃ በድንገት ሰዎችን ቢያጠፋ፣እሱ ንጹሐን ሰዎች በሚደርስባቸው ሥቃይ ያፌዛል። 24  ምድር ለክፉዎች ተሰጥታለች፤+እሱ የዳኞቿን ዓይኖች* ይሸፍናል። ይህን የሚያደርገው እሱ ካልሆነ ታዲያ ማን ነው? 25  ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤+መልካም ነገር ሳያይ ፈጥኖ ይነጉዳል። 26  ከደንገል እንደተሠሩ ጀልባዎች፣የሚያድኑትንም ነገር ለመያዝ ወደ ታች እንደሚወረወሩ ንስሮች ይከንፋል። 27  ‘ብሶቴን እረሳለሁ፤የፊቴን ገጽታ ቀይሬ ደስተኛ እሆናለሁ’ ብል እንኳ፣ 28  ከሥቃዬ ሁሉ የተነሳ አሁንም ፍርሃት ይሰማኛል፤+ንጹሕ ሆኜ እንደማታገኘኝ አውቃለሁ። 29  በደለኛ* ሆኜ መገኘቴ አይቀርም። ታዲያ ለምን በከንቱ እደክማለሁ?+ 30  ከቀለጠ በረዶ በተገኘ ውኃ ብታጠብ፣እጆቼንም በእንዶድ* ባነጻ፣+ 31  አንተ አዘቅት ውስጥ ትነክረኛለህ፤ከዚህም የተነሳ የገዛ ልብሶቼ እንኳ ይጸየፉኛል። 32  መልስ እሰጠው ዘንድ፣ችሎት ፊትም አብረን እንቀርብ ዘንድ እሱ እንደ እኔ ሰው አይደለምና።+ 33  በመካከላችን የሚበይን፣*ሊዳኘንም የሚችል* ሰው የለም። 34  እኔን መምታቱን ቢያቆም፣*ሽብርም ባይለቅብኝ፣+ 35  ያን ጊዜ ያለፍርሃት አናግረዋለሁ፤በፍርሃት የምናገር ሰው አይደለሁምና።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አምላክን ፍርድ ፊት ማቅረብ ቢፈልግ።”
ወይም “ያስወግዳል።”
የታላቁ ድብ ኅብረ ከዋክብት (ኧርሳ ሜጀር) ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “የደቡቡን ውስጠኛ ክፍሎች።”
በቶረስ ኅብረ ከዋክብት የታቀፉ ፐልያዲስ የሚባሉ ከዋክብት ሊሆኑ ይችላሉ።
የኦርዮን ኅብረ ከዋክብት ሊሆን ይችላል።
እጅግ ግዙፍ የሆነ የባሕር ፍጥረት ሊሆን ይችላል።
“ተሟጋቼን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ማን ሊጠራኝ።”
ወይም “ንጹሕ ብሆን እንኳ።”
ቃል በቃል “ጠማማ።”
ወይም “ንጹሕ ብሆን እንኳ።”
ወይም “ነፍሴን አላውቅም።”
ወይም “እንቀዋለሁ፤ እቃወመዋለሁ።”
ወይም “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁትንም።”
ቃል በቃል “ፊቶች።”
ቃል በቃል “ክፉ።”
ወይም “በፖታሽ።”
ወይም “መካከለኛ የሚሆን።”
ቃል በቃል “እጁንም በሁለታችን ላይ የሚጭን።”
ቃል በቃል “በትሩን ከእኔ ላይ ቢያነሳ።”