ዘፍጥረት 19:1-38

  • መላእክት ወደ ሎጥ መጡ (1-11)

  • ሎጥና ቤተሰቡ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ተነገራቸው (12-22)

  • ሰዶምና ገሞራ ጠፉ (23-29)

    • የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ ሆነች (26)

  • ሎጥና ሴቶች ልጆቹ (30-38)

    • የሞዓባውያንና የአሞናውያን መገኛ (37, 38)

19  ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። እሱም ባያቸው ጊዜ ተነስቶ ወደ እነሱ ሄደ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ።+ 2  እንዲህም አለ፦ “ጌቶቼ፣ እባካችሁ ወደ አገልጋያችሁ ቤት ጎራ በሉና እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ። ከዚያም በማለዳ ተነስታችሁ ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” እነሱም መልሰው “አይሆንም፣ አደባባዩ ላይ እናድራለን” አሉ። 3  እሱ ግን አጥብቆ ስለለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ሄዱ። ከዚያም ግብዣ አደረገላቸው። ቂጣም ጋገረላቸው፤ እነሱም በሉ። 4  ከመተኛታቸውም በፊት የከተማዋ ሰዎች ማለትም በሰዶም ያሉ ወንዶች ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ ግልብጥ ብለው በመውጣት ቤቱን ከበቡት። 5  ሎጥንም ደጋግመው በመጥራት “በዚህ ምሽት ወደ አንተ የመጡት ሰዎች የት አሉ? ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ወደ ውጭ አውጣልን” ይሉት ጀመር።+ 6  ከዚያም ሎጥ ወደ እነሱ ወደ ውጭ ወጣ፤ በሩንም ከኋላው ዘጋው። 7  እንዲህም አላቸው፦ “እባካችሁ ወንድሞቼ፣ እንዲህ ያለ ክፉ ድርጊት አትፈጽሙ። 8  እባካችሁ፣ ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እባካችሁ፣ እነሱን ላውጣላችሁና መልካም መስሎ የታያችሁን አድርጉባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን በጣሪያዬ ጥላ* ሥር ስለተጠለሉ በእነሱ ላይ ምንም ነገር አታድርጉ።”+ 9  በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “ዞር በል!” አሉት። ከዚያም “ይህ ወገን የሌለው መጤ፣ ደግሞ በእኛ ላይ ዳኛ ልሁን ይላል እንዴ! በእነሱ ላይ ልናደርግ ካሰብነው የከፋ ነገር እንዳናደርግብህ” አሉት። ሎጥንም በኃይል ገፉት፤ በሩንም ሊሰብሩት ተቃረቡ። 10  ስለሆነም ውስጥ የነበሩት ሰዎች እጃቸውን ወደ ውጭ ዘርግተው ሎጥን እነሱ ወዳሉበት ወደ ቤት አስገቡት፤ በሩንም ዘጉት። 11  ሆኖም በቤቱ ደጃፍ ላይ የነበሩትን ሰዎች ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ አሳወሯቸው፤ በዚህም የተነሳ ሰዎቹ በሩን ለማግኘት ሲዳክሩ ደከሙ። 12  ከዚያም ሰዎቹ ሎጥን እንዲህ አሉት፦ “እዚህ የሚኖሩ ሌሎች ዘመዶች አሉህ? አማቾችህን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚኖር ዘመድ አዝማድህን በሙሉ ከዚህ ስፍራ ይዘህ ውጣ! 13  ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቦቿን በተመለከተ የሚሰማው ጩኸት በይሖዋ ፊት እየጨመረ ስለመጣ+ ይሖዋ ከተማዋን እንድናጠፋት ልኮናል።” 14  በመሆኑም ሎጥ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኛ የሆኑትን አማቾቹን “ተነሱ! ይሖዋ ከተማዋን ሊያጠፋት ስለሆነ ከዚህ ስፍራ ውጡ!” አላቸው። አማቾቹ ግን የሚያሾፍ መሰላቸው።+ 15  ጎህ ሲቀድ መላእክቱ ሎጥን “ተነስ! በከተማዋ በደል የተነሳ እንዳትጠፋ ከአንተ ጋር ያሉትን ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ውጣ!” በማለት አቻኮሉት።+ 16  ሎጥ በዘገየ ጊዜ ይሖዋ ስለራራለት+ ሰዎቹ የእሱን እጅ፣ የሚስቱን እጅና የሁለቱን ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዋ አስወጡት።+ 17  ልክ ከተማዋ ዳርቻ ላይ እንዳደረሷቸውም ከእነሱ አንዱ እንዲህ አለ፦ “ሕይወትህን* ለማትረፍ ሽሽ! ወደ ኋላህ እንዳትመለከት፤+ አውራጃውንም+ ለቀህ እስክትወጣ ድረስ የትኛውም ቦታ ላይ እንዳትቆም! እንዳትጠፋ ወደ ተራራማው አካባቢ ሽሽ!” 18  ከዚያም ሎጥ እንዲህ አላቸው፦ “እባክህ ይሖዋ፣ ወደዚያስ አልሂድ! 19  መቼም አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ አግኝቷል፤ ሕይወቴን* በማትረፍ ታላቅ ደግነት* አሳይተኸኛል፤+ ሆኖም አደጋ እንዳይደርስብኝና እንዳልሞት ስለምፈራ+ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሽቼ ማምለጥ አልችልም። 20  እባክህ ይህች ከተማ ቅርብ ነች፤ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ፤ ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እባክህ፣ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ? ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እንደዚያ ከሆነ እተርፋለሁ።”* 21  እሱም እንዲህ አለው፦ “እሺ ይሁን፣ ያልካትን ከተማ ባለማጥፋት+ አሁንም አሳቢነት አሳይሃለሁ።+ 22  ፍጠን! አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም ነገር ማድረግ ስለማልችል+ ወደዚያ ሽሽ!” ከተማዋን ዞአር*+ ብሎ የሰየማት ለዚህ ነው። 23  ሎጥ ዞአር ሲደርስ ፀሐይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። 24  ከዚያም ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበ፤ ይህም የመጣው ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ ነው።+ 25  እሱም እነዚህን ከተሞች ገለባበጠ፤ አዎ፣ የከተሞቹን ነዋሪዎችና የምድሪቱን ተክል+ ሁሉ ጨምሮ መላውን አውራጃ ገለባበጠ። 26  ሆኖም ከሎጥ በስተ ኋላ የነበረችው የሎጥ ሚስት ወደ ኋላ ዞራ መመልከት ጀመረች፤ እሷም የጨው ዓምድ ሆነች።+ 27  አብርሃምም በማለዳ ተነሳ፤ ቀደም ሲል በይሖዋ ፊት ቆሞ ወደነበረበትም ስፍራ ሄደ።+ 28  ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ እንዲሁም በአውራጃው ውስጥ ወዳሉት ከተሞች በሙሉ ቁልቁል ሲያይም የሚያስገርም ነገር ተመለከተ። ከእቶን እንደሚወጣ ያለ የሚትጎለጎል ጭስ ከምድሩ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር!+ 29  አምላክ የአውራጃውን ከተሞች ባጠፋበት ጊዜ ሎጥ ይኖርባቸው ከነበሩትና አምላክ ካጠፋቸው ከተሞች ውስጥ ሎጥን በማውጣት አብርሃምን አሰበው።+ 30  በኋላም ሎጥ በዞአር+ መኖር ስለፈራ ከዞአር ወጥቶ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራማው አካባቢ መኖር ጀመረ።+ ስለዚህ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ መኖር ጀመረ። 31  የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “አባታችን አርጅቷል፤ በመላው ምድር ላይ ባለው ልማድ መሠረት ከእኛ ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ በዚህ አካባቢ የለም። 32  ነይ፣ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእሱ ጋር እንተኛ፤ እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።” 33  በመሆኑም በዚያ ምሽት አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ ገብታ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። 34  በማግስቱም የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “ይኸው እኔ ትናንት ሌሊት ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ። ዛሬ ማታም የወይን ጠጅ እናጠጣው። ከዚያም አንቺ ገብተሽ ከእሱ ጋር ትተኚያለሽ። እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።” 35  በመሆኑም በዚያ ምሽትም አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ታናሽየዋ ልጅ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሳ አላወቀም። 36  ስለሆነም ሁለቱም የሎጥ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። 37  ታላቅየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ+ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት ሞዓባውያን አባት ነው።+ 38  ታናሽየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት አሞናውያን አባት ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከለላ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ታማኝ ፍቅር።”
ወይም “ነፍሴ በሕይወት ትኖራለች።”
“ትንሽነት” የሚል ትርጉም አለው።