ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 3:1-17

  • የመጨረሻዎቹ ቀኖች (1-7)

  • የጳውሎስን ምሳሌ በጥብቅ መከተል (8-13)

  • ‘በተማርካቸው ነገሮች ጽና’ (14-17)

    • “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው” (16)

3  ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀናት+ ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። 2  ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ 3  ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣* ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ 4  ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ 5  ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ፤+ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 6  በየቤቱ ሾልከው የሚገቡ ሰዎች የሚነሱት ከእነዚህ መካከል ነው፤ እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ምኞቶች የሚነዱትን፣ በኃጢአት የተተበተቡትን ደካማ ሴቶች ይማርካሉ፤ 7  እንደነዚህ ያሉት ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ሆኖም ትክክለኛውን የእውነት እውቀት መረዳት አይችሉም። 8  እንግዲህ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደተቃወሙት ሁሉ እነዚህም እውነትን ይቃወማሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ የተበላሸ ከመሆኑም ሌላ በእምነት ጎዳና ስለማይመላለሱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል። 9  ይሁንና የእነዚያ ሁለት ሰዎች ሞኝነት ለሰው ሁሉ በጣም ግልጽ እንደነበረ ሁሉ የእነዚህ ሰዎች ሞኝነትም ግልጽ ስለሚሆን በአካሄዳቸው ብዙም ሊገፉበት አይችሉም።+ 10  አንተ ግን ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣+ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን በጥብቅ ተከትለሃል፤ 11  እንደ አንጾኪያ፣+ ኢቆንዮንና+ ልስጥራ+ ባሉ ቦታዎች የደረሰብኝን ስደትና መከራ ታውቃለህ። ይህን ሁሉ ስደት በጽናት አሳልፌአለሁ፤ ጌታም ከዚህ ሁሉ ታደገኝ።+ 12  በእርግጥም የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።+ 13  ሆኖም ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።+ 14  አንተ ግን በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር፤+ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ ታውቃለህ፤ 15  እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት+ ከጨቅላነትህ+ ጀምሮ አውቀሃል።+ 16  ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤+ እንዲሁም ለማስተማር፣+ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና* በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ፤+ 17  ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለሰው ፍቅር የሌላቸው።”
ወይም “ለማረምና።”