በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንት ዘመን መጋቢዎች ምን ሚና ነበራቸው?

በጥንት ዘመን አንድ መጋቢ የሌላን ሰው ቤት ወይም ንብረት ያስተዳድር ነበር። “መጋቢ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የበላይ ተመልካችን ወይም ቤት የሚያስተዳድር ሰውን ሊያመለክቱ ይችላሉ።

የያዕቆብ ልጅ የሆነው ዮሴፍ፣ ግብፅ ውስጥ ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታው ቤት ላይ መጋቢ ሆኖ ያገለግል ነበር። እንዲያውም ግብፃዊ ጌታው “ያለውን ነገር ሁሉ ለዮሴፍ በኃላፊነት [ሰጥቶት]” ነበር። (ዘፍ. 39:2-6) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዮሴፍ ራሱ ግብፅ ውስጥ ኃያል ገዢ በሆነ ጊዜ በራሱ ቤት ላይ መጋቢ ሾሟል።—ዘፍ. 44:4

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ባለርስቶች አብዛኛውን ጊዜ ከእርሻቸው ርቀው ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በመሆኑም ባለርስቶቹ፣ የቀን ሠራተኞች በየዕለቱ በእርሻቸው ላይ የሚያከናውኑትን ሥራ የሚቆጣጠሩ መጋቢዎች ይሾሙ ነበር።

መጋቢ ሆኖ ለመሾም የሚያስፈልገው ብቃት ምን ነበር? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ካልየሜላ የተባለ ሮማዊ ጸሐፊ፣ የበላይ ተመልካች ወይም መጋቢ ሆኖ የሚሾም ባሪያ “ሥራውን በደንብ እንደሚያከናውን ያስመሠከረ ሰው” መሆን እንዳለበት ተናግሯል። ግለሰቡ ‘ሥልጣኑን ጭካኔ በማይንጸባረቅበት መንገድ መጠቀም ቢኖርበትም በጣም ልል ሊሆን አይገባም።’ ካልየሜላ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉ የበለጠ ደግሞ፣ የማያውቀውን ነገር አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ መሆን የለበትም፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ለመማር የሚጓጓ እንዲሆን ይጠበቅበታል።”

የአምላክ ቃል በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን አንዳንድ ሥራዎች ለመግለጽ መጋቢነትን እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን ‘የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ [ከአምላክ ያገኙትን ስጦታ] አንዳቸው ሌላውን ለማገልገል እንዲጠቀሙበት’ አበረታቷቸዋል።—1 ጴጥ. 4:10

ኢየሱስም በሉቃስ 16:1-8 ላይ የአንድን መጋቢ ምሳሌ ጠቅሷል። በተጨማሪም ንጉሥ ሆኖ የሚገኝበትን ጊዜ ስለሚጠቁመው ምልክት በተናገረው ትንቢት ላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወይም “ታማኝና ልባም መጋቢ” እንደሚሾም ለተከታዮቹ ቃል ገብቷል። የዚህ መጋቢ ዋነኛ ኃላፊነት፣ በመጨረሻው ዘመን ለክርስቶስ ተከታዮች የማያቋርጥ መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ ነው። (ማቴ. 24:45-47፤ ሉቃስ 12:42) እኛም ታማኙ መጋቢ የሚያዘጋጃቸውንና በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ ሰዎች የሚያቀርባቸውን እምነት የሚያጠናክሩ ጽሑፎች ማግኘት እንችላለን፤ ለዚህም በጣም አመስጋኞች ነን።