ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?
ለሌሎች አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ውጥረት የነገሠባቸውን ሁኔታዎች ለማርገብ ያስችላል፤ እንዲሁም አለመግባባቶች እንዳይባባሱ ያደርጋል።
-
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) አክብሮት የጎደለው አነጋገርና ድርጊት እሳት ላይ ጭድ እንደመጨመር ነው፤ የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።
-
ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ. 12:34) አክብሮት የጎደለው አነጋገር በልባችን ውስጥ ሥር የሰደደ ችግር እንዳለ ይኸውም ከእኛ የተለየ ዘር፣ ጎሳ፣ ብሔር ወይም የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች መጥፎ አመለካከት እንዳለን ሊጠቁም ይችላል።
በቅርቡ ከ28 አገሮች በተውጣጡ ከ32,000 የሚበልጡ ሰዎች ላይ አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር። በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት የአሁኑን ያህል መከባበር የጠፋበት ዘመን አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ለሁሉም ሰዎች አክብሮት አሳይ፤ አመለካከታቸውን ባትጋራም እንኳ ልታከብራቸው ይገባል። ሊያግባቧችሁ የሚችሉ ነጥቦችን ፈልግ። ይህም ነቃፊ ከመሆን ወይም በእነሱ ላይ ከመፍረድ እንድትቆጠብ ይረዳሃል።
ሌሎች እንዲይዙህ በምትፈልግበት መንገድ ሰዎችን ያዝ። ሌሎችን በአሳቢነትና በፍትሕ የምትይዝ ከሆነ እነሱም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርጉልህ ይችላሉ።
ይቅር ባይ ሁን። ሌሎች አክብሮት የጎደለው ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉ ሆን ብለው እንዳደረጉት ከማሰብ ይልቅ በቸልታ ለማለፍ ሞክር።
ምን ጥረት እያደረግን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች በመኖሪያ አካባቢያቸውም ሆነ በሥራ ቦታቸው መከባበር እንዲሰፍን ጥረት ያደርጋሉ።
ለሁሉም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እናስተምራለን። ሆኖም እምነታችንንም ሆነ አመለካከታችንን እንዲቀበሉ አናስገድድም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል መልእክታችንን “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን።—1 ጴጥሮስ 3:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24
ለአድልዎ ቦታ የለንም። አስተዳደጋቸውና ባሕላቸው ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስን መማር ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ክፍት ናቸው። መቻቻል እንዲሰፍን ጥረት እናደርጋለን፤ እንዲሁም ‘ሁሉንም ዓይነት ሰው እናከብራለን።’—1 ጴጥሮስ 2:17
የመንግሥትን ሥልጣን እናከብራለን። (ሮም 13:1) ሕጉን እንታዘዛለን፤ እንዲሁም ግብር እንከፍላለን። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ብንሆንም ሌሎች ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው እንገነዘባለን፤ ይህን መብታቸውንም እናከብራለን።