የሌሎችን ጠንካራ ጎን ለማስተዋል ሞክር
እንዲህ አለማድረግ ምን ችግር አለው?
ኩራት ጭፍን ጥላቻ እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። ኩሩ የሆነ ሰው ለራሱ የተጋነነ አመለካከት አለው። ራሱን ከሌሎች አስበልጦ የሚመለከት ሲሆን ከእሱ የተለዩ ሰዎች የእሱ የበታች እንደሆኑ አድርጎ ያስባል። ማንም ሰው በዚህ ወጥመድ ሊያዝ ይችላል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “መጠኑ ይነስ ይብዛ እንጂ አብዛኞቹ ባሕሎች የእነሱ ምግብ፣ አኗኗር፣ አለባበስ፣ ልማድ፣ አመለካከት፣ እሴት፣ ወዘተ ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል።” ታዲያ እንዲህ ያለውን የተዛባ አስተሳሰብ ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ
“ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3
ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከልክ ያለፈ ኩራትን ለማስወገድ የእሱ ተቃራኒ የሆነውን ባሕርይ ማለትም ትሕትናን ማዳበር ያስፈልገናል። ትሕትና በአንዳንድ ነገሮች ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ነው ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል አንድ ቡድን ሊኖር አይችልም።
የሽቴፋንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሽቴፋን ያደገው በአንድ የኮሚኒስት አገር ውስጥ ሲሆን ኮሚኒስት ባልሆኑ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ጭፍን ጥላቻ ነበረው። በኋላ ላይ ግን ይህን ስሜቱን ማስወገድ ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ጭፍን ጥላቻን ለማስወገድ የሚረዳው ትልቁ ነገር ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጎ ማሰብ እንደሆነ አምናለሁ። ሁሉንም ነገር አውቃለሁ ማለት አልችልም። ከእያንዳንዱ ሰው የሆነ ነገር መማር እችላለሁ።”
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስለ ራስህ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርግ። አንዳንድ ጉድለቶች እንዳሉብህ አትዘንጋ። አንተ ደካማ በሆንክባቸው አንዳንድ አቅጣጫዎች ሌሎች ጠንካራ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምነህ ተቀበል። በአንድ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ሰዎች በሙሉ ተመሳሳይ ድክመት እንዳለባቸው አድርገህ አታስብ።
አንድ ሰው የሆነ ቡድን አባል ስለሆነ ብቻ ስለ እሱ አሉታዊ አመለካከት ከመያዝ ይልቅ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦
አንተ ደካማ በሆንክባቸው አንዳንድ አቅጣጫዎች ሌሎች ጠንካራ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምነህ ተቀበል
-
‘የዚህን ሰው አንዳንድ ባሕርያት የምጠላው በእርግጥ መጥፎ ስለሆኑ ነው ወይስ እኔ ከለመድኩት የተለዩ ስለሆኑ?’
-
‘ይህ ሰው በእኔስ ላይ ጉድለት ሊያገኝ አይችልም?’
-
‘ይህ ሰው ከእኔ የተሻለ የሆነባቸው አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?’
ለእነዚህ ጥያቄዎች በሐቀኝነት መልስ መስጠትህ በውስጥህ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ እንድታስወግድ ብቻ ሳይሆን ስለዚያ ሰው የምታደንቃቸው አንዳንድ ነገሮች እንድታገኝም ይረዳሃል።