በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርኪኦሎጂ ግኝቶች መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋሉ?

የአርኪኦሎጂ ግኝቶች መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋሉ?

የአርኪኦሎጂ ግኝቶች መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋሉ?

በአርኪኦሎጂ የጥናት መስክ የሚደረገው ምርምር ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያስገኘው ጥቅም አለው። ይህንን የምንለው በዚህ የምርምር መስክ የሚገኙት ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበረው የሰዎች አኗኗር እንዲሁም ስለተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች ያላቸውን እውቀት ስለሚጨምርላቸው ነው። በተጨማሪም አርኪኦሎጂ ባቢሎንን፣ ነነዌንና ጢሮስን የመሳሰሉ የጥንት ከተሞችን አወዳደቅ በሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተነገሩት ትንቢቶች አፈጻጸም ጠቃሚ መረጃዎችን ይሰጣል። (ኤርምያስ 51:37፤ ሕዝቅኤል 26:4, 12፤ ሶፎንያስ 2:13-15) በዚህ የጥናት መስክ ሙሉ በሙሉ እንዳንተማመንበት የሚያደርጉን ነገሮች አሉ። በቁፋሮ የሚገኙት ጥንታዊ ቁሳቁሶች ስለምንነታቸው ትንታኔ ሊሰጥባቸው ይገባል፤ የሚሰጡት ትንታኔዎች ግን ስህተት ሊኖርባቸው እንዲሁም እንደ ተመራማሪዎቹ አመለካከት ሊለያዩ ይችላሉ።

የክርስትና እምነት በተሰባበሩ የሸክላ ጌጦች፣ በበሰበሱ ጡቦች ወይም በተናዱ ግምቦች ላይ የተመካ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የተሟላና እርስ በርሱ ስምምነት ያለው መንፈሳዊ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:7፤ ዕብራውያን 11:1) በእርግጥም ‘ቅዱሳን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ ለመጻፋቸው’ አሳማኝ ማስረጃ የሚሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሐሳቦች እርስ በርስ ያላቸው ስምምነት፣ የጸሐፊዎቹ ግልጽነት፣ በውስጡ ያሉት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ዘገባዎች ትክክል መሆናቸውን የሚያረጋግጡና ትኩረታችንን የሚስቡ በርካታ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶችን መመልከታችን ጥሩ ነው።

በ1970 ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲቆፍሩ የነበሩ አርኪኦሎጂስቶች አንድ የተቃጠለ የሕንፃ ፍርስራሽ አገኙ። የቡድኑ መሪ የነበሩት ነማን አቪጋድ “የሚታየው ነገር ምንነት በሙያው ለሠለጠነ ሰው በጣም ግልጽ ነበር” በማለት ጽፈዋል። “ሕንፃው በእሳት የጋየ ሲሆን ግድግዳዎቹና ጣሪያው ተደርምሰዋል።” በአንደኛው ክፍል ውስጥ ደረጃውን ለመያዝ የተዘረጉ የአንድ እጅ አጥንቶች [1] ተገኝተዋል።

በወለሉ ላይ ሳንቲሞች [2] ተበታትነው የተገኙ ሲሆን ከመካከላቸው የቅርብ ነው የሚባለው አይሁዳውያን በሮማ መንግሥት ላይ ባመጹ በአራተኛው ዓመት ማለትም በ69 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተሠራ እንደሆነ ተገምቷል። ሕንፃው ከመደርመሱ በፊት ዕቃዎች ተበታትነው ነበር። አቪጋድ “ይህን ስናይ ጆሴፈስ ከተማይቱ ድል ከተደረገች በኋላ የሮማ ወታደሮች በየቤቱ እየገቡ ይዘርፉ እንደነበረ የሰጠው መግለጫ ትዝ አለን” በማለት ተናግረዋል። ታሪክ ጸሐፊዎች፣ ሮማውያን ኢየሩሳሌምን የዘረፉትና የደመሰሱት በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መሆኑን ይናገራሉ።

ተንታኞች በአንደኛው ክፍል ውስጥ የተገኙት አጥንቶች በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረች የአንዲት ሴት እጅ መሆናቸውን አመልክተዋል። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው እንዲህ ይላል:- “ሮማውያን ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ በእሳት በተያያዘው ቤት ማዕድ ቤት ውስጥ የነበረች አንዲት ወጣት ሴት እሳቱ ድንገት ደርሶባት ወለሉ ላይ ወደቀች፤ የሞተችው በራፉ አጠገብ ወዳለው ደረጃ ለመድረስ በመፍጨርጨር ላይ እያለች ነበር። እሳቱ በፍጥነት በመዛመቱ ምክንያት . . . ልታመልጥ ስላልቻለች በፍርስራሹ ተቀብራለች።”

ይህ ክስተት ኢየሱስ ወደ 40 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ ተናግሮት የነበረውን ትንቢት ያስታውሰናል:- “ጠላቶችሽ . . . አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም።”—ሉቃስ 19:43, 44

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸው ሐሳቦች ትክክል መሆናቸውን ከሚያረጋግጡት አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች መካከል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ የአንዳንድ ግለሰቦች ስሞች ይገኙበታል። ከእነዚህ ግኝቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸው አንዳንድ ሰዎች ጸሐፊዎቹ የፈጠሯቸው እንደሆኑ ወይም ደግሞ ዝናቸውን አጋንነው እንደጻፉላቸው አድርገው ሲናገሩ የነበረውን ሐሳብ ውድቅ የሚያደርጉ ናቸው።

ተቀርጸው የተገኙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስሞች

በአንድ ወቅት ታዋቂ ምሑራን በኢሳይያስ 20:1 ላይ በስም የተጠቀሰው የአሦር ንጉሥ ዳግማዊ ሳርጎን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በሕይወት የኖረ ሰው እንዳልሆነ ይሰማቸው ነበር። ይሁን እንጂ በ1843 ኢራቅ ውስጥ በዛሬዋ ኮርሰባድ አቅራቢያ የጤግሮስ ገባር በሆነ አንድ ወንዝ አጠገብ የሳርጎን ቤተ መንግሥት [3] ተገኘ። ቤተ መንግሥቱ ያለበት ሥፍራ 10 ሄክታር ይሸፍናል። በዓለም ታሪክ የማይታወቅ የነበረው ዳግማዊ ሳርጎን በአሁኑ ጊዜ በጣም ከታወቁት የአሦር ነገሥታት አንዱ ሆኗል። ስለ እሱ ከሚናገሩት ዜና ታሪኮች [4] መካከል በአንዱ ላይ የእስራኤል ከተማ የነበረችውን ሰማርያን በቁጥጥሩ ሥር እንዳደረገ ተናግሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ሰማርያ በአሦራውያን እጅ የወደቀችው በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። በተጨማሪም ሳርጎን አሽዶድን በቁጥጥሩ ሥር እንዳደረገ የመዘገበ ሲሆን ይህም በኢሳይያስ 20:1 ላይ ከተጠቀሰው ሌላ ሐሳብ ጋር ይስማማል።

አርኪኦሎጂስቶች በዛሬዋ ኢራቅ ውስጥ ትገኝ የነበረችውን የጥንቷን ባቢሎን ከተማ ፍርስራሽ ሲቆፍሩ በኢሽታር በር አጠገብ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ 300 የሚያህሉ ጽላቶች አገኙ። በጽላቶቹ ላይ የሰፈሩት ጽሑፎች ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር የግዛት ዘመን የሚናገሩ ሲሆን ከእነዚህ ስሞች መካከል “ያውኪን፣ የያሁድ ምድር ንጉሥ” የሚለው ይገኝበታል። ይህ ስም ናቡከደነፆር በ617 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌምን መጀመሪያ በያዘበት ወቅት ማርኮ ወደ ባቢሎን የወሰደውን የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን የሚያመለክት ነው። (2 ነገሥት 24:11-15) በጽላቶቹ ላይ አምስቱ የዮአኪን ወንዶች ልጆችም ተጠቅሰዋል።—1 ዜና መዋዕል 3:17, 18

በ2005 አርኪኦሎጂስቶች የንጉሥ ዳዊትን ቤተ መንግሥት እናገኛለን ብለው ባሰቡበት ቦታ ላይ ሲቆፍሩ ከ2,600 ዓመታት በፊት የአምላክ ነቢይ በነበረው በኤርምያስ ዘመን ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ድምጥማጧን ባጠፉበት ወቅት እንደፈራረሰ ያመኑበትን የሕንፃ ፍርስራሽ አገኙ። ሕንፃው የዳዊት ቤተ መንግሥት ይሁን አይሁን በውል አልታወቀም። ይሁን እንጂ ኤላት ማሳር የተባሉ አንዲት አርኪኦሎጂስት ከፍርስራሹ ውስጥ “የሾቪ ልጅ፣ የሸሌምያሁ ልጅ የየሁካል ንብረት” የሚል 1 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው የሸክላ ማኅተም [5] አገኙ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሸክላው ላይ ያረፈው ማኅተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤርምያስን እንደተቃወመ የተነገረለት የሁካል (ጀሁካል ወይም ዮካል) የተባለ አንድ አይሁዳዊ ባለ ሥልጣን ማኅተም ነበር።—ኤርምያስ 37:3፤ 38:1-6

የሁካል በዳዊት ከተማ ውስጥ በአንድ የሸክላ ማኅተም ላይ ስሙ ከተገኘው ከሳፋን ልጅ ከገማርያ ቀጥሎ “በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን” እንደነበረ ማሳር ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሸሌምያ (ሸሌምያሁ) ልጅ የሁካል የይሁዳ መስፍን እንደነበረ ይጠቁማል። ይህ ማኅተም ከመገኘቱ በፊት ዮካል መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ውጭ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አልነበረም።

እስራኤላውያን ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ማንበብና መጻፍ ይችሉ እንደነበረ ያመለክታል። (ዘኍልቍ 5:23፤ ኢያሱ 24:26፤ ኢሳይያስ 10:19) ይሁን እንጂ ተቺዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በአብዛኛው ይተላለፍ የነበረው በቃል እንደነበረ በመግለጽ ይህን ሐሳብ ይቃወማሉ። ሆኖም በ2005 በኢየሩሳሌምና በሜድትራንያን መካከል በሚገኘው ቴል ዛይት በሚባል ቦታ ሲቆፍሩ የነበሩ አርኪኦሎጂስቶች እስካሁን ከተገኙት ሁሉ እጅግ ጥንታዊ ሳይሆን እንደማይቀር የሚገመት በበሃ ድንጋይ ላይ የተቀረጸ የዕብራይስጥ የፊደል ገበታ [6] ሲያገኙ የተቺዎቹ አስተያየት ውድቅ ሆነ።

አንዳንድ ምሑራን እንደሚናገሩት፣ በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተሠራ የሚገመተው ይህ ግኝት እስራኤላውያን “መደበኛ የሆነ የጸሐፊነት ሥልጠና፣” “የተራቀቀ ባሕል” እና “ኢየሩሳሌም ውስጥ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር” እንደነበራቸው ይጠቁማል። ስለዚህ ተቺዎች ከሚሉት በተቃራኒ ቢያንስ ቢያንስ በአሥረኛው መቶ ዘመን እስራኤላውያን የተማሩና ታሪካቸውን መመዝገብ ይችሉ የነበረ ይመስላል።

የአሦራውያን የታሪክ መዛግብት ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናሉ

በአንድ ወቅት ኃያል መንግሥት የነበረችው አሦር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰች ሲሆን በዚህች አገር የተገኙ በርካታ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቷ አሦር ዋና ከተማ በነበረችው በነነዌ በተደረገ ቁፋሮ ለኪሶ በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦራውያን እጅ በወደቀች ጊዜ የአሦር ወታደሮች አይሁዳውያን ምርኮኞችን እየነዱ ወደ ግዞት ሲወስዷቸው የሚያሳይ ሥዕል የተቀረጸበት አንድ ጥርብ ድንጋይ [7] በንጉሥ ሰናክሬም ቤተ መንግሥት ውስጥ ተገኝቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በሚመለከት የሚናገረውን ታሪክ በ2 ነገሥት 18:13-15 ላይ ማንበብ ትችላለህ።

በነነዌ የተገኘው የሰናክሬም ዜና ታሪክ [8] በስም ጠቅሶ በሚናገርለት በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ሰናክሬም ያደረገውን ወታደራዊ ዘመቻ ይገልጻል። በሌሎች ገዢዎች የተዘጋጁ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ ጽላቶች የይሁዳ ነገሥታት የነበሩትን አካዝንና ምናሴን እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት የነበሩትን ዖምሪን፣ ኢዩን፣ ኢዮአስን፣ ምናሔምንና ሆሴዕን ይጠቅሳሉ።

ሰናክሬም በታሪክ ዘገባው ላይ ስላገኛቸው ወታደራዊ ስኬቶች ተኩራርቶ ቢናገርም ኢየሩሳሌምን እንደያዘ አለመጠቀሱ ልብ ሊባል ይገባዋል። ይህም ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመውጋት እንዳልከበባት ከዚህ ይልቅ በአምላክ እጅ ድል እንደተደረገ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚያ በኋላ ውርደት የተከናነበው ሰናክሬም ወደ ነነዌ ተመልሶ የገዛ ልጆቹ እንደገደሉት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 37:33-38) የሚገርመው በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ሁለት የአሦራውያን ጽሑፎች ሰናክሬም በሰው እጅ መገደሉን ያረጋግጣሉ።

የይሖዋ ነቢያት የነበሩት ናሆምና ሶፎንያስ ነነዌ በሕዝቦቿ ክፋት የተነሳ ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስ ትንቢት ተናግረው ነበር። (ናሆም 1:1፤ ከ2:8 እስከ 3:19፤ ሶፎንያስ 2:13-15) የባቢሎን ንጉሥ ናቦፖላሳርና ሜዶናዊው ሲያክስሬዝ ኃይላቸውን አስተባብረው ነነዌን በከበቧትና በኋላም በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድል ባደረጓት ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ነነዌ መገኘቷና ፍርስራሿ ተቆፍሮ መውጣቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው የሚገኙት ታሪኮች ትክክል መሆናቸውን ያረጋግጣል።

ከጤግሮስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፣ ከነነዌ ደግሞ በስተ ደቡብ ምሥራቅ ትገኝ የነበረችው ኑዚ የተባለችው ጥንታዊት ከተማ ከ1925 ጀምሮ እስከ 1931 ባሉት ዓመታት በቁፋሮ በወጣችበት ጊዜ 20,000 የሸክላ ጽላቶችን ጨምሮ በርካታ ጥንታዊ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል። በባቢሎናውያን ቋንቋ የተጻፉ ጽሑፎች ያሉባቸው እነዚህ ጽላቶች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጸው የአበው ዘመን ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሕግ ነክ ጉዳዮችን ጨምሮ ብዙ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጽሑፎቹ አብዛኛውን ጊዜ በሰው አምሳል ከሸክላ ይሠሩ የነበሩትና እንደ ቤተሰብ አማልክት የሚታዩት ትንንሽ ጌጠኛ ቅርጻ ቅርጾች ባለንብረቱ የውርስ መብት እንዳለው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ሆነው ያገለግሉ እንደነበር ያመለክታሉ። ይህ ባሕል የእምነት አባት የሆነው የያዕቆብ ቤተሰብ ወደ ሌላ ሥፍራ ለመሄድ በተነሳበት ወቅት ሚስቱ ራሔል የአባቷን የላባን የቤተሰብ አማልክት ወይም “ተራፊም” የወሰደችበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል። ከሁኔታው መረዳት እንደምንችለው ላባ ተራፊሙን መልሶ ለማግኘት ሞክሮ ነበር።—ዘፍጥረት 31:14-16, 19, 25-35 የ1954 ትርጉም

የኢሳይያስ ትንቢት እና የቂሮስ ሲሊንደር

እዚህ ገጽ ላይ በሚታየው ጥንታዊ ሞላላ ሸክላ ላይ ተቀርጾ የሚገኘው ጽሑፍ አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትክክል መሆኑን ያረጋግጥልናል። የቂሮስ ሲሊንደር [9] በመባል የሚታወቀው ይህ ሰነድ የተገኘው ከባግዳድ 32 ኪሎ ሜትር ርቃ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ በምትገኘው ሲፓር በተባለች ጥንታዊ ከተማ ነው። ሰነዱ ባቢሎን የፋርስ ግዛት መሥራች በነበረው በታላቁ ቂሮስ ድል መደረጓን ይናገራል። የሚገርመው ይህ ከመፈጸሙ ከ200 ዓመታት ቀደም ብሎ ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ቂሮስ ተብሎ ስለሚጠራ የሜዶ ፋርስ ገዢ “እርሱ እረኛዬ ነው፤ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል፤ ኢየሩሳሌምም፣ ‘“እንደ ገና ትሠራ”፣ ቤተ መቅደሱም፣ “መሠረቱ ይጣል” ይላል’ እላለሁ” የሚል ትንቢት አስነግሮ ነበር።—ኢሳይያስ 13:1,17-19፤ 44:26 እስከ 45:3

በሸክላው ላይ ያለው ጽሑፍ ቂሮስ ከጥንት ገዢዎች ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከዚያ በፊት የነበረው ኃያል መንግሥት ይዟቸው የነበሩ ምርኮኞችን ወደ ትውልድ አገራቸው ስለመመለስ ያስነገረውን አዋጅ የሚጠቅስ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው። ቂሮስ አይሁዶችን ነፃ እንዳወጣቸውና ኢየሩሳሌምን መልሰው እንደገነቡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የዓለም ታሪክ ይመሠክራሉ።—2 ዜና መዋዕል 36:23፤ ዕዝራ 1:1-4

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ምርምር የሚያደርገው የአርኪኦሎጂ የጥናት መስክ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አዲስ ቢሆንም በጣም ጠቃሚ መረጃዎችን ያስገኘ ትልቅ የምርምር ዘርፍ ሆኗል። ከላይ እንደተመለከትነው በቁፋሮ የተገኙ በርካታ ግኝቶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ታሪኮች ጥቃቅን በሚመስሉ ዝርዝር ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር እውነተኛና ትክክል መሆናቸውን ይመሠክራሉ።

ለተጨማሪ መረጃ

መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ የሰፈነበትና ዓላማ ያለው ሕይወት እንድትኖር ሊረዳህ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ—የእውነትና የትንቢት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) የተሰኘው የሁለት ሰዓት ዲቪዲ ይህን ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳይ የሚያካትት ሲሆን ቀልብ የሚስቡ ቃለ ምልልሶችንም ይዟል።—ፊልሙ በ32 ቋንቋዎች ይገኛል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?

መጽሐፍ ቅዱስ ከተረት የጸዳና እርስ በርሱ የማይጋጭ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ማግኘት ትፈልጋለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ተአምራት በእርግጥ የተፈጸሙ ናቸው? በዚህ ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ አማካኝነት ሐቁን መመርመር ትችላለህ።—ይህ መጽሐፍ በ56 ቋንቋዎች ታትሟል።

[ምንጭ]

ታላቁ እስክንድር:- Roma, Musei Capitolini

ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዳ ታስቦ በተዘጋጀው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት 19 ምዕራፎች ጎላ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን የሚዳስሱ ከመሆናቸውም በላይ አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ዘር ምን ዓላማ እንዳለው ያብራራሉ።—ይህ መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ በ162 ቋንቋዎች ይገኛል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ

በተለይ ለልጆች የተዘጋጀውና ማራኪ ሥዕሎች ያሉት ይህ መጽሐፍ ስለ 116 ሰዎችና ክንውኖች ይናገራል፤ ሁሉም ታሪኮች የቀረቡት በተፈጸሙበት የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ነው።—መጽሐፉ በ194 ቋንቋዎች ይገኛል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሳንቲሞች:- Generously Donated by Company for Reconstruction & Development of Jewish Quarter, Jerusalem Old City

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Society for Exploration of Land of Israel and its Antiquities

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

3: Musée du Louvre, Paris; 4: Photograph taken by courtesy of the British Museum; 5: Gabi Laron/Institute of Archaeology/Hebrew University © Eilat Mazar

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

6: AP Photo/Keith Srakocic; 7, 8: Photograph taken by courtesy of the British Museum

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum