“ጥቅስን ከጥቅስ ጋር እናወዳድር”
አንድ ሰው ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ እየሄደ ሳለ አንድ ትራክት ባቡር ውስጥ ወድቆ አገኘ። ትራክቱ ‘የሰው ነፍስ ሟች ነች’ ይላል። በሜቶዲስት ኤፒስኮፖል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ የሆነው ይህ ሰው ሐሳቡ ስለሳበው ማንበብ ጀመረ። ከዚያ ቀደም የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት ሙሉ በሙሉ ያምንበት ስለነበር ባነበበው ነገር ተደነቀ። በዚያን ጊዜ ትራክቱን ማን እንደጻፈው አያውቅም ነበር። ያም ቢሆን ግን በጽሑፉ ውስጥ የቀረበው የመከራከሪያ ነጥብ አሳማኝና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ ትምህርቱ ጥልቅ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ እንደሆነ ተሰማው።
ይህ አገልጋይ ጆርጅ ስቶርዝ ሲሆን ወቅቱ 1837 ነበር። ቻርልስ ዳርዊን ከጊዜ በኋላ ላመነጨው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የሆኑትን ነጥቦች በጽሑፍ ያሰፈረውም በዚሁ ዓመት ነበር። በዚያን ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖታዊ የነበሩ ሲሆን በአምላክ ላይም እምነት ነበራቸው። ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ከመሆኑም በላይ ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር።
ከጊዜ በኋላ ስቶርዝ ትራክቱን የጻፈው በፊላደልፊያ፣ ፔንስልቬንያ ይኖር የነበረው ሄንሪ ግሩ እንደሆነ አወቀ። ግሩ “ቅዱስ ጽሑፉን ለመተርጎም የሚረዳ ከራሱ የተሻለ [መሣሪያ] የለም” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አጥብቆ ይከተል ነበር። ግሩ እና ባልደረቦቹ ሕይወታቸውንም ሆነ ማንኛውንም እንቅስቃሴያቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር አስማምተው የመኖርን ዓላማ በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር። በጥናታቸው አማካኝነት ግሩም የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ለማግኘት ችለዋል።
ግሩ የጻፋቸው ነገሮች፣ ስቶርዝ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ነፍስ ምን እንደሚሉ በጥንቃቄ እንዲመለከትና ጉዳዩን አብረውት ከሚያገለግሉት ጋር ሆኖ እንዲወያይበት አነሳስተውታል። ስቶርዝ ለአምስት ዓመታት ጥልቀት ያለው ጥናት ካደረገ በኋላ አዲስ ያገኘውን ውድ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ለሕዝብ ለማሳወቅ ወሰነ። በመጀመሪያ በ1842 አንድ እሁድ ዕለት ሃይማኖታዊ ስብከት የሚቀርብበት ዝግጅት አደረገ። ሆኖም ትምህርቱን በሚገባ ለማብራራት ተጨማሪ የስብከት ፕሮግራሞች ማዘጋጀት እንዳለበት ተሰማው። በመጨረሻም የሰው ነፍስ ሟች እንደሆነች ለማብራራት ያዘጋጃቸውን ስድስት የስብከት ፕሮግራሞች ሲክስ ሴርመንስ በሚል ርዕስ አሳተማቸው። ስቶርዝ ሕዝበ ክርስትና በምታስተምራቸው አምላክን የማያስከብሩ መሠረተ ትምህርቶች ውስጥ ተደብቀው የሚገኙት አስደሳች እውነቶች ተሸፍነው እንዳይቀሩ ጥቅሶችን ከጥቅሶች ጋር በጥንቃቄ አወዳድሯል።
መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ እንደማትሞት ያስተምራል?
የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ላሳዩት ታማኝነት ያለመሞት ባሕርይ ሽልማት ሆኖ እንደሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:50-56) አለመሞት ለታማኞች የሚሰጥ ሽልማት ከሆነ ክፉዎች የማትሞት ነፍስ ልትኖራቸው አትችልም በማለት ስቶርዝ አስረድቷል። ይህን ጉዳይ በተመለከተም እንዲሁ ግምታዊ አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማገናዘብ ሞክሯል። በማቴዎስ 10:28 ላይ የሚገኘውን “ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ” የሚለውን ጥቅስ መርምሯል። ስለዚህ ነፍስ ልትጠፋ ትችላለች። ከዚህም በተጨማሪ በሕዝቅኤል 18:4 ላይ የሚገኘውን “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” የሚለውን ጥቅስም ተመልክቷል። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲመለከተው ውድ የሆነው እውነት ግልጽ ሆኖ ታየው። ስቶርዝ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ያለኝ እምነት ትክክል ከሆነ፣ [ነፍስ አትሞትም በሚለው] የተለመደ ጽንሰ ሐሳብ ተሸፍነው የነበሩት አብዛኞቹ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ግልጽ፣ ማራኪና ትርጉም የሚሰጡ ከመሆናቸውም በላይ ኃይል ይኖራቸዋል።”
ሆኖም እንደ ይሁዳ 7 ያሉ ጥቅሶችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኛነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል።” አንዳንዶች ይህንን ጥቅስ ሲያነቡ በሰዶምና ገሞራ የጠፉት ሰዎች ነፍሳት በዘላለም እሳት እየተቀጡ ነው ብለው ሊደመድሙ ይችላሉ። ስቶርዝ “ጥቅስን ከጥቅስ ጋር እናወዳድር” በማለት ጽፏል። ከዚያም በ2 ጴጥሮስ 2:5, 6 ላይ የሚገኘውን “ኖኅን . . . አድኖ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣ ደግሞም ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው” የሚለውን ሐሳብ ጠቀሰ። አዎን፣ ሰዶምና ገሞራ ከነዋሪዎቻቸው ጋር ለዘላለም ጠፍተው አመድ ሆነዋል።
ስቶርዝ እንዲህ በማለት አስረድቷል:- “ጴጥሮስ በይሁዳ [መጽሐፍ] ላይ ተጨማሪ ብርሃን ፈንጥቆልናል። ሁለቱም መጻሕፍት አምላክ በኃጢአተኞች እንደማይደሰት ማሳየቱን ግልጽ በሆነ መንገድ ያስቀምጡታል። . . . በአሮጌው ዓለም ማለትም በሰዶምና ገሞራ ላይ የተወሰደው የፍርድ እርምጃ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ የሚሆን ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ወይም ‘ዘላለማዊ’ ተግሣጽ፣ ማስጠንቀቂያ አሊያም ‘ምሳሌ’ ነው።” ስለዚህ ይሁዳ ዘላለማዊ እንደሆነ የገለጸው ሰዶምና ገሞራን ያጠፋው እሳት ያስከተለውን ውጤት ነው። ይህ ደግሞ የሰው ነፍስ ትሞታለች የሚለውን እውነት አይቀይረውም።
ስቶርዝ አመለካከቱን የሚደግፉለትን ጥቅሶች ብቻ እየመረጠ አልተጠቀመም። ከዚህ ይልቅ በእያንዳንዱ ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብና የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ጭብጥ ይመለከት ነበር። እንዲሁም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከሌሎቹ ጥቅሶች ጋር የሚጋጭ መስሎ ከታየው ትክክለኛውን ሐሳብ ለማግኘት የተቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይመለከት ነበር።
ራስል በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ያደረገው ጥናት
ከጆርጅ ስቶርዝ ጋር ከነበሩት መካከል በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ያቋቋመ አንድ ወጣት ይገኝበታል። እርሱም ቻርልስ ቴዝ ራስል ይባላል። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተው የራስል የመጀመሪያ ጽሑፍ ስቶርዝ በሚያዘጋጀው ባይብል ኤግዛሚነር በተባለው መጽሔት ላይ በ1876 ታተመ። ራስል የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደሩበት ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ አዘጋጅ የሆነው ራስል፣ ስቶርዝ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ሐሳብ በመስጠት ያደረገለትን እርዳታ ያደንቅ ነበር።
ቻርልስ ቴዝ ራስል በ18 ዓመቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን በማቋቋም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። ከራስል ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የነበረው አሌክሳንደር ማክሚላን ዝግጅቱን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ጥያቄ ያነሳና [ቡድኑ] ይወያይበታል። ከነጥቡ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ጥቅሶች በሙሉ ይመለከታሉ፤ ከዚያም ጥቅሶቹ እርስ በርሳቸው የሚስማሙ መሆናቸውን ካመኑ በኋላ የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍሩታል።”
ራስል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በአጠቃላይ ሲታይ እርስ በርሱም ሆነ የቅዱስ ጽሑፉ ባለቤት የሆነው አምላክ ካሉት ባሕርያት ጋር የሚስማማና የማይለዋወጥ መሆን አለበት የሚል አመለካከት ነበረው። በተጨማሪም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ይብራራል የሚል እምነት ነበረው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለው ልማድ
ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲተረጉሙ ማድረግ በራስል፣ በስቶርዝ ወይም በግሩ የተጀመረ ነገር አይደለም። ይህን ዘዴ የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ይሠራበት ነበር። የአንድን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም ግልጽ ለማድረግ በርካታ ጥቅሶችን ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዛሙርቱ በሰንበት እሸት ቀጥፈው በመብላታቸው ምክንያት ፈሪሳውያን ባወገዟቸው ጊዜ ኢየሱስ በ1 ሳሙኤል 21:6 ላይ ያለውን ዘገባ በመጥቀስ የሰንበት ሕግ እንዴት በሥራ ላይ መዋል እንደሚገባው ገለጸላቸው። የሃይማኖት መሪዎቹ፣ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች የተቀደሰውን ኅብስት እንደበሉ የሚናገረውን ዘገባ ያውቁት ነበር። ኢየሱስ በመቀጠል ኅብስቱን መብላት የሚችሉት የአሮን ዘር የሆኑት ካህናት ብቻ መሆናቸውን የሚናገረውን የሕጉን ክፍል ጠቀሰላቸው። (ዘፀአት 29:32, 33፤ ዘሌዋውያን 24:9) እንደዚያም ሆኖ ዳዊት ኅብስቱን እንዲበላ ተፈቅዶለታል። ኢየሱስ ይህን አሳማኝ ነጥብ ሲደመድም ከሆሴዕ መጽሐፍ በመጥቀስ “‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 12:1-8) አንድን ነገር በትክክል ለመረዳት ሲባል ጥቅሶችን ከሌሎች ጥቅሶች ጋር በማወዳደር ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
የኢየሱስ ተከታዮችም የአንድን ጥቅስ ትርጉም ለመረዳት ሌሎች ጥቅሶችን በመጠቀም ረገድ የኢየሱስን ፈለግ ተከትለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት ሰዎች ሲሰብክ ‘ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር፣ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ ያረጋግጥ [“ማስረጃ እያቀረበ ያብራራላቸውና ያስረዳቸው፣” NW]’ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3) ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፋቸው ደብዳቤዎችም ላይ አንድን ጥቅስ ለማብራራት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ፣ ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ መሆኑን ለመግለጽ በርካታ ጥቅሶችን ተጠቅሟል።—ዕብራውያን 10:1-18
አዎን፣ በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖሩ የነበሩ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ፈለግ ተከትለዋል። ጥቅሶችን ከሌሎች ጥቅሶች ጋር የማወዳደር ልማድ ወይም ወግ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይም ይሠራበታል። (2 ተሰሎንቄ 2:15 የ1954 ትርጉም) የይሖዋ ምሥክሮች አንድን ጥቅስ በሚመረምሩበት ጊዜ ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ይጠቀማሉ።
በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመልከት
መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ የኢየሱስንና የታማኝ ተከታዮቹን ግሩም ምሳሌ ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ግምት ውስጥ እናስገባለን። የጥቅሱን ትርጉም ለመረዳት በዙሪያው ያለው ሐሳብ የሚረዳን እንዴት ነው? በምሳሌ ለማስረዳት፣ ኢየሱስ በማቴዎስ 16:28 ላይ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት እንመልከት:- “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት ሰዎች መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” አንዳንዶች፣ ኢየሱስ ይህንን ሲናገር በአጠገቡ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በሙሉ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከመቋቋሙ በፊት ስለሞቱ እነዚህ ቃላት አልተፈጸሙም ሊሉ ይችላሉ። እንዲያውም ዚ ኢንተርፕሬተርስ ባይብል ይህንን ጥቅስ በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ትንቢቱ አልተፈጸመም፣ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች ይህ ጥቅስ ዘይቤያዊ አነጋገር መሆኑን መግለጽ አስፈልጓቸው ነበር።”
ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብም ሆነ በማርቆስና በሉቃስ ላይ የሚገኙት ተመሳሳይ ዘገባዎች የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም እንድንረዳ ያስችሉናል። ማቴዎስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ካሰፈረ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ።” (ማቴዎስ 17:1, 2) ማርቆስም ሆነ ሉቃስ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የተናገራቸውን ቃላት በተአምራዊ መንገድ ከመለወጡ ጋር አያይዘው ገልጸውታል። (ማርቆስ 9:1-8፤ ሉቃስ 9:27-36) ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን መምጣቱ በሦስቱ ሐዋርያት ፊት በተአምራዊ ሁኔታ ተለውጦ በክብር በተገለጠ ጊዜ ታይቷል። ጴጥሮስ ‘የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ኀይልና መምጣት’ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ከማየቱ ጋር አያይዞ መግለጹ ሐሳቡን በዚህ መንገድ መረዳታችን ትክክል መሆኑን ያረጋግጥልናል።—2 ጴጥሮስ 1:16-18
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም ታደርጋለህ?
በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ብትመለከትም የአንድን ጥቅስ ትርጉም ለመረዳት ባትችልስ? የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ጭብጥ በአእምሮህ በመያዝ ጥቅሱን ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ማወዳደርህ ሊረዳህ ይችላል። ይህን ለማድረግ የሚረዳ ግሩም መሣሪያ፣ በአሁኑ ጊዜ በሙሉም ሆነ በከፊል በ57 ቋንቋዎች በተዘጋጀው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን
ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ይገኛል። አብዛኞቹ የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች በየገጹ መሃል ላይ የሚገኝ ማጣቀሻ አላቸው። በርከት ባሉ ዋና ዋና ቋንቋዎች በሚገኘው ባለማጣቀሻ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ከ125,000 በላይ የሚሆኑ ማጣቀሻዎችን ማግኘት ትችላለህ። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “መግቢያ” እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የማጣቀሻ ጥቅሶቹን በጥንቃቄ ማመሳከርም ሆነ አብረው የቀረቡትን የግርጌ ማስታወሻዎች መመርመር 66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ያላቸውን ስምምነት ግልጽ ከማድረጉም በላይ እነዚህ መጽሐፎች በአንድነት ተዳምረው በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዳስገኙ ለማስተዋል ያስችላል።”ጥቅሶችን ለመረዳት እንድንችል ማጣቀሻዎች የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እየተመለከትን እንሄዳለን። የአብራም ወይም የአብርሃምን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አብራምና ቤተሰቡ ከዑር ሲወጡ በግንባር ቀደምትነት ይመራቸው የነበረው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ እናንሳ። ዘፍጥረት 11:31 እንዲህ ይላል:- “ታራ ልጁን አብራምን፣ . . . ሎጥን እንዲሁም . . . ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነዓን ለመሄድ በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ከዑር አብረው ወጡ፤ ነገር ግን ካራን በደረሱ ጊዜ በዚያ ተቀመጡ።” አንድ ሰው ይህንን ጥቅስ በማንበብ ብቻ የአብራም አባት ታራ ቤተሰቡን ይመራ እንደነበር ሊናገር ይችላል። ሆኖም በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ከዚህ ጥቅስ ጋር ተያይዘው የቀረቡ 11 ማጣቀሻዎችን እናገኛለን። የመጨረሻው የማጣቀሻ ጥቅስ ወደ የሐዋርያት ሥራ 7:2 ይመራናል፤ እዚያ ላይ እስጢፋኖስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች እንዲህ ብሏል:- “አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፤ ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 7:2, 3) እስጢፋኖስ አብራም ከካራን ሲወጣ የነበረውን ሁኔታ ከዑር ከመውጣቱ ጋር አምታቶት ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም ይህም ቢሆን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ነው።—ዘፍጥረት 12:1-3
ታዲያ በዘፍጥረት 11:31 ላይ “ታራ ልጁን አብራምን” እንዲሁም የቤተሰቡን ሌሎች አባላት ይዞ ከዑር እንደወጣ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው? በዚያን ጊዜ ታራ የቤተሰቡ መሪ ነበር። በመሆኑም ከአብራም ጋር ለመውጣት በመስማማቱ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ካራን እንደሄደ ተደርጎ ተገልጿል። እነዚህን ሁለት ጥቅሶች በማወዳደርና ለማስማማት በመሞከር ምን እንደተከናወነ መረዳት እንችላለን። አብራም በአምላክ መመሪያ መሠረት ከዑር መውጣት እንዳለባቸው ለአባቱ በአክብሮት በመንገር አሳምኖታል።
ቅዱሳን ጽሑፎችን በምናነብበት ጊዜ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብና የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ጭብጥ በአእምሯችን መያዝ አለብን። ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል:- “ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው። እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው።” (1 ቆሮንቶስ 2:11-13) ቃሉን ለመረዳት እንድንችል ይሖዋን መለመን ይገባናል፤ እንዲሁም በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በማንበብና ተዛማጅ የሆኑ ጥቅሶችን ፈልጎ በመመርመር ‘መንፈሳዊ እውነትን በመንፈሳዊ ቃል ለመግለጽ’ መጣር ይኖርብናል። የአምላክን ቃል በማጥናት በጣም ውድ የሆነውን እውነት ለማግኘት መፈለጋችንን እንቀጥል።