በእምነታቸው ምሰሏቸው
“እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ”
ዲቦራ በታቦር ተራራ ላይ የተሰበሰቡትን ወታደሮች እየተመለከተች ነው። ወታደሮቹን እዚያ ስታይ በውስጧ ልዩ ስሜት አደረባት። በዚያ ማለዳ ስለ ወታደሮቹ ጀግንነትና መሪያቸው ባርቅ ስላሳየው እምነት እያሰላሰለች ነው። እነዚህ 10,000 ወታደሮች በዚህ ዕለት እምነታቸውና ድፍረታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይፈተናል። በቁጥርም ሆነ በትጥቅ ከሚበልጣቸው በጣም ጨካኝ ከሆነ የጠላት ሠራዊት ጋር ፊት ለፊት ይፋጠጣሉ። ያም ሆኖ ይህች ሴት በሰጠቻቸው ማበረታቻ እዚህ ተገኝተዋል።
ዲቦራና ባርቅ ቁልቁል አሻግረው እየተመለከቱ ሳለ ነፋሱ የዲቦራን ልብስ ሲያውለበልበው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የታቦር ተራራ ሾጠጥ ብሎ አናቱ ጠፍጠፍ ያለ ነው። ከተራራው አናት ላይ ሆኖ 400 ሜትር ዝቅ ብሎ የሚገኘውን በስተ ደቡብ ምዕራብ የተንጣለለውን የኤዝድራኢሎንን ሜዳ ቁልቁል መመልከት ይቻላል። እየተጥመዘመዘ የሚፈሰው የቂሾን ወንዝ ለጥ ያለውን መስክ አቋርጦ በቀርሜሎስ ተራራ ግርጌ ወደ ታላቁ ባሕር ይፈሳል። የቂሾን ወንዝ ያን ዕለት ደረቅ የነበረ ቢሆንም በተንጣለለው ሜዳ ላይ የሚያብረቀርቅ ነገር ይታያል። የተለያዩ የብረት መሣሪያዎችን የታጠቀው የሲሳራ ሠራዊት እየቀረበ ነው። ኃያል ተዋጊዎችን ያቀፈው የሲሳራ ሠራዊት በመንኮራኩራቸው ላይ የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው 900 ሠረገላዎች አሉት። ሲሳራ በቂ ትጥቅ የሌለውን የእስራኤል ሠራዊት እንደ እህል አጭዶ ለመደምሰስ ቆርጧል።
ዲቦራ፣ ባርቅም ሆነ አብሮት ያለው ሠራዊት እሷ አንድ ነገር እንድትላቸው ማለትም የሆነ ምልክት እንድትሰጣቸው እንደሚጠብቁ ታውቅ ነበር። በዚያ ያለችው ሴት እሷ ብቻ ናት? እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ይህን ዓይነት ከባድ ኃላፊነት መሸከሟ ምን ስሜት አሳድሮባታል? እዚያ የተገኘችበት ዓላማ ግራ ገብቷት ይሆን? ግራ እንዳልገባት ከሁኔታው በግልጽ መረዳት ይቻላል። አምላኳ የሆነው ይሖዋ ይህን ጦርነት እንድታስጀምር ነግሯታል፤ አንዲትን ሴት ተጠቅሞ ጦርነቱ እንዲደመደም እንደሚያደርግም ገልጾላታል። (መሳፍንት 4:9) ከዲቦራም ሆነ ከእነዚህ ደፋር ተዋጊዎች በአምላክ ላይ እምነት ስለማሳደር ምን እንማራለን?
“ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት”
መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲቦራን የሚያስተዋውቀን ‘ነቢዪት’ በማለት ነው። ለዲቦራ የተሰጣት ይህ ስያሜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እምብዛም ያልተለመደ ነው፤ ይህ ሲባል ግን እንዲህ ዓይነቱ ስያሜ የተሰጣት እሷ ብቻ ነች ማለት አይደለም። * ዲቦራ ሌላም ኃፊነት ነበራት። በእስራኤላውያን መካከል ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ይሖዋ የሚሰጣትን መልስ ተጠቅማ አለመግባባቶችን ትፈታ ነበር።—መሳፍንት 4:4, 5
ዲቦራ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ፣ በቤቴልና በራማ መካከል ባለው ስፍራ ትኖር ነበር። በዚያም በአንድ የዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ይሖዋ በሚሰጣት መመሪያ መሠረት ሕዝቡን ታገለግል ነበር። የተጣለባት ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ እሙን ነው፤ ሆኖም ይህ ኃላፊነት ከአቅሟ በላይ ሆኖ እንዲታያት አላደረገችም። እሷ የምትሰጠው አገልግሎት የግድ አስፈላጊ ነበር። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ በመንፈስ መሪነት አንድ መዝሙር የማቀናበር መብት አግኝታለች፤ በመዝሙሩም ላይ “እነሱ አዳዲስ አማልክትን መረጡ፤ በበሮቹም ላይ ጦርነት ነበር” በማለት ታማኝ ስላልነበሩት ሕዝቦቿ የሚናገር ሐሳብ ጠቅሳለች። (መሳፍንት 5:8) እስራኤላውያን ይሖዋን ትተው ሌሎች አማልክትን ማምለክ ስለጀመሩ ይሖዋ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር። የከነአን ንጉሥ ያቢን፣ ሲሳራ በተባለው ኃያል የጦር መሪ አማካኝነት እስራኤላውያንን ይገዛ ነበር።
ሲሳራ! ስሙ ብቻ እንኳ ሲጠራ በእስራኤል ውስጥ ሽብር ይነግሣል። የከነአናውያን ሃይማኖትና ባሕል በጭካኔ ድርጊት የተሞላ ሲሆን ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብንና በቤተ መቅደስ ውስጥ ዝሙት መፈጸምን ይጨምር ነበር። ከነአናዊ የሆነ መሳፍንት 5:6, 7) ሰዎች በግብርና ሥራ መሰማራትም ሆነ ቅጥር በሌላቸው መንደሮች ውስጥ መኖር በመፍራት በየጥሻውና በየኮረብታው ውስጥ ተሸሽገው ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ጥቃት ሊሰነዘርብን፣ ልጆቻችንን ልንነጠቅ እንዲሁም ሴቶቻችን ሊደፈሩ ይችላሉ በሚል ስጋት በጎዳናዎች ላይ እንደ ልብ ከመጓዝ ተቆጥበው እንደሚሆን መገመት እንችላለን። *
የጦር አዛዥና ሠራዊቱ የእስራኤልን ምድር ማስተዳደሩ በሕዝቡ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር? በምድሪቱ ላይ እንደ ልብ መዘዋወር አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ መንደሮቹ ሁሉ ጭር ብለው እንደነበር ዲቦራ ካቀናበረችው መዝሙር መረዳት ይቻላል። (ይሖዋ አንገተ ደንዳና የነበሩት ሕዝቦቹ ለመለወጥ ፈቃደኞች መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እስኪያገኝ ድረስ ወይም “እኔ ዲቦራ እስክነሳ ድረስ፣ እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳ ድረስ” የሚለው ዲቦራና ባርቅ የዘመሩት በመንፈስ መሪነት የተጻፈው መዝሙር እስኪፈጸም ድረስ ለ20 ዓመት በእስራኤል ውስጥ ሽብር ነግሦ ነበር። የላጲዶት ሚስት የነበረችው ዲቦራ ቃል በቃል የልጆች እናት የነበረች ትሁን አትሁን የምናውቀው ነገር የለም፤ ይሁንና ይህ አባባል የተሠራበት በምሳሌያዊ ሁኔታ ነው። ይሖዋ፣ ዲቦራ እንደ እናት ሆና ብሔሩን እንድትታደግ ኃላፊነት የሰጣት ያህል ነው። ደፋር የእምነት ሰው የሆነውን መስፍኑን ባርቅን ጠርታ በሲሳራ ላይ እንዲዘምት መመሪያ እንድትሰጠው ይሖዋ ተልእኮ ሰጥቷት ነበር።—መሳፍንት 4:3, 6, 7፤ 5:7
ይሖዋ በዲቦራ አማካኝነት “ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ባርቅ ከሁለቱም የእስራኤል ነገዶች 10,000 ሰዎች መሰብሰብ ነበረበት። ዲቦራ የባርቅ ሠራዊት ኃያል የሆነውን ሲሳራንና 900 ሠረገላዎቹን ድል እንደሚያደርግ አምላክ የገባውን ቃል ነገረችው! አምላክ የገባው ይህ ቃል ባርቅን ሳያስገርመው አልቀረም። እስራኤላውያን፣ የጦር ሠራዊትም ሆነ ትጥቅ የላቸውም ቢባል ይቀላል። ያም ሆኖ ባርቅ ወደ ጦርነቱ ለመውጣት ተስማማ፤ ይሁንና እንዲህ የሚያደርገው ዲቦራ አብራው ወደ ታቦር ተራራ የምትወጣ ከሆነ ብቻ ነው።—መሳፍንት 4:6-8፤ 5:6-8
አንዳንዶች ባርቅ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማቅረቡ እምነት የለሽ መሆኑን ያሳያል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፤ ሆኖም ይህ ከእውነታው የራቀ ነው። ምክንያቱም አምላክን የጠየቀው ተጨማሪ የጦር መሣሪያ እንዲሰጠው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ባርቅ የእምነት ሰው እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ ወኪል የሆነችው ዲቦራ አብራቸው መሆኗ እሱንም ሆነ ሠራዊቱን ሊያበረታታቸው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። (ዕብራውያን 11:32, 33) ይሖዋም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶታል። ባርቅ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ዲቦራ አብራው እንድትሄድ ፈቅዷል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በጦርነቱ የሚገኘው ድል የሚያመጣው ክብር ለወንድ እንደማይሰጥ ዲቦራ በመንፈስ መሪነት ትንቢት እንድትናገርም አድርጓል። (መሳፍንት 4:9) አምላክ ክፉ የሆነው ሲሳራ በሴት እጅ እንዲወድቅ አስቀድሞ ወስኗል!
በዛሬው ጊዜ በሴቶች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍ፣ ዓመፅና ጥቃት ይፈጸማል። አምላክ ለእነሱ እንዲሰጥ የሚፈልገውን ክብር ሮም 2:11፤ ገላትያ 3:28) በተጨማሪም ይሖዋ ለሴቶች ኃላፊነት በመስጠት እንዲሁም እንደሚተማመንባቸውና ሞገሱን እንደሚያሳያቸው የሚያረጋግጡ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ በማድረግ እንደሚባርካቸው ከዲቦራ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። በዚህ ዓለም ተስፋፍቶ የሚገኘው በሴቶች ላይ የሚፈጸም መድልዎ በእኛም አመለካከት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ አለብን።
የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው። ሆኖም አምላክ ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን በእኩል ዓይን የሚመለከታቸው ከመሆኑም ሌላ በፊቱ ሞገስ ማግኘት ይችላሉ። (“ምድር ተናወጠች፤ ሰማያትም ውኃ አወረዱ”
ባርቅ ሠራዊቱን ለመሰብሰብ ሄደ። አስፈሪውን የሲሳራን ሠራዊት የሚገጥሙ 10,000 ደፋር ተዋጊዎችን ሰበሰበ። ባርቅ ሠራዊቱን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ በወጣበት ጊዜ እነሱን የሚያደፋፍርበት መንገድ በማግኘቱ ተደስቷል። ምክንያቱም ‘ዲቦራም አብራው እንደወጣች’ እናነባለን። (መሳፍንት 4:10) ሠራዊቱ ወደ ታቦር ተራራ ሲወጣ ይህች ደፋር ሴት አብራቸው መሆኗ ወታደሮቹን ምን ያህል እንዳደፋፈራቸው መገመት ትችላለህ! ዲቦራ ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ከእነሱ ጋር ለመሄድ የተነሳችው በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ስለነበራት ነው።
ሲሳራ እስራኤላውያን በእሱ ላይ ለመዝመት ሠራዊታቸውን እንዳሰባሰቡ ሲያውቅ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። በርካታ ከነአናውያን ነገሥታት፣ ምናልባትም ከእነሱ በኃይል ከሚልቀው ከንጉሥ ያቢን ጋር ሠራዊታቸውን አስተባበሩ። የሲሳራ ሠራዊት የሚነዳው ብዛት ያለው ሠረገላ አንድ ላይ ሲጓዝ ምድር የተናወጠች ይመስላል። ከነአናውያን ምስኪን የሆነውን የእስራኤል ሠራዊት በቅጽበት እንደሚደመስሱት እርግጠኞች ነበሩ።—መሳፍንት 4:12, 13፤ 5:19
ጠላት ወደ እነሱ እየቀረበ ሲመጣ ባርቅና ዲቦራ ምን ያደርጉ ይሆን? እዚያው ታቦር ተራራ ላይ ቢቆዩ ወደ እነሱ እየቀረበ የመጣውን የከነአናውያን ጦር ለመመከት የተሻለ አጋጣሚ ይኖራቸዋል፤ ምክንያቱም ሠረገላዎቹ እንደ ልብ ማጥቃት የሚችሉት ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ነው። ይሁንና ባርቅ ውጊያውን የሚያካሂደው ይሖዋ በሚሰጠው አመራር መሠረት ስለሆነ ዲቦራ የምትለውን ለመስማት እየጠበቀ ነበር። በመጨረሻም ዲቦራ “ይሖዋ ሲሳራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ይህ ስለሆነ ተነስ! ይሖዋ በፊትህ ቀድሞ ይወጣ የለም?” በማለት ተናገረች። ከዚያም ባርቅ “10,000 ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ።”—መሳፍንት 4:14 *
የእስራኤል ሠራዊት ከተራራው ላይ ግር ብሎ ለጥ ወዳለው ሜዳ በመውረድ አስፈሪ የጦር መሣሪያ ወደታጠቁት ከነአናውያን በቀጥታ አመራ። ዲቦራ በተናገረችው መሠረት ይሖዋ በፊታቸው ቀድሞ ወጥቶ ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። ዘገባው “ምድር ተናወጠች፤ ሰማያትም ውኃ አወረዱ” ይላል። እብሪተኛ የሆነው የሲሳራ ሠራዊት ግራ ተጋባ። ዝናቡም ያወርደው ጀመር! ዶፍ ዝናብ ስለዘነበ መሬቱ ወዲያውኑ ጨቀየ። ብዙ የብረት መሣሪያ የተገጠመላቸው ሠረገላዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዘነ። ጭቃ ውስጥ ተቀርቅረው መንቀሳቀስ አቃታቸው።—መሳፍንት 4:14, 15፤ 5:4
ባርቅና ሠራዊቱ ዶፍ ዝናብ በመጣሉ አልተደናገጡም። ይህ ሊሆን የቻለው ለምን እንደሆነ ገብቷቸዋል። ቀጥታ ወደ ከነአናውያን ሠራዊት እየገሰገሱ ሄዱ። የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ሆነው እያገለገሉ የነበሩት እስራኤላውያን ከሲሳራ ሠራዊት ውስጥ አንድም ሰው በሕይወት አላስተረፉም። የቂሾን ወንዝ ሞልቶ አስከሬኖቹን በሙሉ ጠራርጎ ወደ ታላቁ ባሕር ወሰዳቸው።—መሳፍንት 4:16፤ 5:21
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አገልጋዮቹን ቃል በቃል ወደ ጦር ሜዳ አይልካቸውም። ይሁንና ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ውጊያ እንዲዋጉ ይጠብቅባቸዋል። (ማቴዎስ 26:52፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4) ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ አምላክን ለመታዘዝ ጥረት ካደረግን በዚህ ውጊያ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው። በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ጎን ለመቆም የሚመርጡ ሰዎች ከባድ ስደት ስለሚያጋጥማቸው ደፋሮች መሆን ያስፈልገናል። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ አልተለወጠም። በእሱ ላይ ከፍተኛ እምነት የነበራቸውን በጥንቷ እስራኤል የነበሩትን ዲቦራን፣ ባርቅንና ደፋር የሆኑትን ወታደሮች እንደታደጋቸው ሁሉ ዛሬም በእሱ የሚታመኑትን ይታደጋቸዋል።
“ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተባረከች”
ከእስራኤላውያን ጠላቶች አንዱ ያውም ቀንደኛው አመለጠ! የአምላክን ሕዝቦች ይጨቁን የነበረው ሲሳራ ከጦር ሜዳው በእግር ሸሽቶ አመለጠ። ሠራዊቱን እዚያው ማጡ ውስጥ ትቶ የራሱን ሕይወት ለማትረፍ የእስራኤል ወታደሮች ሳያዩት ወዳልጨቀየው አካባቢ አመራ፤ ከዚያም በቅርብ አሉኝ ብሎ ወዳሰባቸው ወዳጆቹ ሄደ። የእስራኤል ወታደሮች እንዳያገኙት በጣም በመፍራቱ አውላላ ሜዳውን አቋርጦ ወደ ቄናዊው ሄቤር ድንኳን አመራ፤ ቄናዊው ሄቤር በስተ ደቡብ በዘላንነት ከሚኖሩት ወገኖቹ ተለይቶ በመሄድ ከንጉሥ ያቢን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መሥርቶ ይኖር ነበር።—መሳፍንት 4:11, 17
እጅግ ዝሎ የነበረው ሲሳራ ሄቤር ወደሰፈረበት ቦታ ደረሰ። በወቅቱ ሄቤር ቤት አልነበረም። የሄቤር ሚስት ኢያዔል ግን ቤት
ነበረች። ሲሳራ፣ ኢያዔል ባለቤቷ ከንጉሥ ያቢን ጋር የነበረውን ጥሩ ግንኙነት አስባ እንደምትረዳው ተማምኖ ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። አንዲት ሴት ከባለቤቷ የተለየ አቋም ወይም አመለካከት ይኖራታል ብሎ ሊያስብ አይችልም። ሆኖም ሲሳራ ኢያዔልን አያውቃትም ነበር ማለት እንችላለን! ከነአናውያን ይፈጽሙት የነበረውን አስከፊ ጭቆና ጠንቅቃ ታውቃለች፤ በተጨማሪም በፊቷ ሁለት ምርጫ እንደተደቀነ ተገንዝባ ሊሆን ይችላል። ይህን ክፉ ሰው መርዳት አሊያም ደግሞ የአምላክ ሕዝቦች ጠላት የሆነውን ይህን ሰው በማስወገድ ከይሖዋ ጎን መቆም ትችላለች። ታዲያ ምን ታደርግ ይሆን? አንዲት ሴት ይህን ከፍተኛ ልምድ ያለው ኃያል ተዋጊ ድል ልታደርገው የምትችለው እንዴት ነው?ኢያዔል ምን እርምጃ እንደምትወስድ በፍጥነት መወሰን ነበረባት። እሷም ሲሳራ ገብቶ አረፍ እንዲል ጋበዘችው። ማንም ሰው እሱን ፈልጎ ቢመጣ እዚያ መኖሩን እንዳትናገር አዘዛት። ጋደም ሲል ብርድ ልብስ አለበሰችው፤ የሚጠጣ ውኃ ሲጠይቃትም ወተት ሰጠችው። ወዲያው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያም ኢያዔል በድንኳን የሚኖሩ ሴቶች አዘውትረው የሚጠቀሙባቸውን ሁለት መሣሪያዎች ይኸውም ካስማና መዶሻ ይዛ መጣች። ራስጌው አጠገብ በርከክ ብላ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን አስፈሪ እርምጃ ልትወስድ ነው። በዚህ ጊዜ ለቅጽበት እንኳ ብታመነታ ወይም ፈራ ተባ ብትል ከባድ መዘዝ ሊያስከትልባት ይችላል። ታዲያ ይህን እርምጃ የወሰደችው ይህ ሰው ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስላደረሰው ጭቆና አስባ ይሆን? ወይስ ከይሖዋ ጎን መቆም ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ አስባ? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚለው ነገር የለም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ወዲያውኑ እርምጃ መውሰዷንና ሲሳራ መገደሉን ነው!—መሳፍንት 4:18-21፤ 5:24-27
በመጨረሻም ሲሳራን የገባበት ገብቶ ለመያዝ ቆርጦ የነበረው ባርቅ መጣ። ኢያዔል ካስማው ሰሪሳራዎቹ ላይ ተቸንክሮ የሞተውን ሲሳራን ስታሳየው ባርቅ፣ ዲቦራ የተናገረችው ትንቢት እንደተፈጸመ አወቀ። ሲሳራን የመሰለ ኃያል ተዋጊ በአንዲት ሴት እጅ ወደቀ! በዘመናችን ያሉ ተቺዎች ለኢያዔል ብዙ ዓይነት መጥፎ ስም ቢሰጧትም ባርቅና ዲቦራ ግን ለእሷ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። ኢያዔል በፈጸመችው የጀግንነት ተግባር የተነሳ በመንፈስ መሪነት በዘመሩት መዝሙር ላይ “ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተባረከች ነች” ሲሉ አወድሰዋታል። (መሳፍንት 4:22፤ 5:24) ዲቦራ ምን ዓይነት መንፈስ እንዳሳየች ልብ በል። ኢያዔል እንዲህ ዓይነት ውዳሴ በማግኘቷ አልተመቀኘችም፤ ከዚህ ይልቅ እሷን በዋነኝነት ያሳሰባት የይሖዋ ቃል ፍጻሜውን ማግኘቱ ነው።
ሲሳራ ተገደለ፤ የንጉሥ ያቢን ኃያል ክንድም ተሰበረ። በመጨረሻም ከነአናውያን በእስራኤላውያን ላይ ያደርሱት የነበረው ጭቆና አበቃ። ከዚያ በኋላ ምድሪቱ ለ40 ዓመት ሰላም አገኘች። (መሳፍንት 4:24፤ 5:31) ዲቦራ፣ ባርቅና ኢያዔል በይሖዋ አምላክ በመታመናቸው ምንኛ ተባርከዋል! እኛም ልክ እንደ ዲቦራ በድፍረት ከይሖዋ ጎን የምንቆምና ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የምናደፋፍር ከሆነ ይሖዋ ድልና ዘላቂ ሰላም በመስጠት ይባርከናል።
^ አን.7 እንደ ሚርያም፣ ሕልዳና እና የኢሳይያስ ሚስት ያሉ ሌሎች ሴት ነቢያትም ነበሩ።—ዘፀአት 15:20፤ 2 ነገሥት 22:14፤ ኢሳይያስ 8:3
^ አን.9 ሲሳራ አብዛኛውን ጊዜ ከውጊያ ሲመለስ ልጃገረዶችን፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለእያንዳንዱ ወታደር ከአንድ በላይ ልጃገረዶች ማርኮ ይመጣ እንደነበር ዲቦራ ካቀናበረችው መዝሙር መረዳት ይቻላል። (መሳፍንት 5:30) እዚህ ጥቅስ ላይ “ልጃገረድ” የሚለው ቃል “ማህፀን” የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ይህ አገላለጽ እነዚህ ሴቶች የሚፈለጉት ለፆታ ግንኙነት ብቻ እንደነበር ይጠቁማል። ሴቶችን አስገድዶ መድፈር የተለመደ ነበር።
^ አን.17 የተካሄደው ጦርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል፤ አንደኛው በመሳፍንት ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘው ትረካ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምዕራፍ 5 ላይ የሚገኘው ዲቦራና ባርቅ የዘመሩት መዝሙር ነው። አንደኛው ዘገባ በሌላኛው ላይ ያልተጠቀሰ ዝርዝር ሐሳብ ስለያዘ ሁለቱ ዘገባዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው።