ጆርጂ ፖርኩልያን | የሕይወት ታሪክ
“ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ሕይወቴን በሙሉ ብርታት ሆኖኛል”
ገና በ23 ዓመቴ በማጋዳን፣ ሳይቤሪያ ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ ካምፕ ተላክሁ፤ አካባቢው ለኑሮ ፈጽሞ የማይመች ነበር። ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ ገና አንድ ዓመቴ ነበር። ተሞክሮ አልነበረኝም፤ በዚያ ላይ ችኩል ነበርኩ። በመሆኑም ለአንድ እስረኛ ስለ አዲሱ እምነቴ ለመናገር ያደረግሁት የመጀመሪያ ሙከራ ጠብ ውስጥ ሊከተኝ ነበር።
ለመሆኑ የኮሚኒዝም አራማጅ የነበርኩት ሰው የመንግሥት ጠላት ተብሎ የተፈረጀን ሃይማኖታዊ ቡድን እንድቀላቀል ያነሳሳኝ ምንድን ነው? በጉልበት ሥራ ካምፕና በግዞት በቆየሁባቸው ዓመታት የይሖዋ ፍቅርና ሥልጠና ባሕርዬን እንዳሻሽል የረዳኝስ እንዴት ነው?
ፍትሕና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ያደረግኩት ፍለጋ
በ1930 ታባኒ ውስጥ ተወለድኩ፤ በሰሜን ሞልዶቫ የምትገኝ የድሆች መንደር ናት። ወላጆቼ ስድስት ልጆቻቸውን ለማሳደግ በግብርና ሥራ ደፋ ቀና ይሉ ነበር። ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ ነበር። እናቴ ኦርቶዶክስ ስትሆን አባቴ ደግሞ ካቶሊክ ነበር። የቀሳውስቱን አሳፋሪ ምግባር እያነሱ ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቁ ነበር።
በ18 ዓመቴ ትምህርት ስጨርስ የኮሚኒዝም ትምህርቶችን የሚያራምድ የወጣቶች ድርጅት ተቀላቀልኩ፤ ይህ ድርጅት ኮምሶሞል ተብሎ ይጠራል። ዓላማውም እጩ የኮሚኒስት ፓርቲ አባላትን መመልመል ነው። ብዙም ሳይቆይ የአካባቢያችን ቡድን ጸሐፊ ሆኜ እንድሠራ ተመረጥኩ። ወንድማማችነት፣ እኩልነትና ፍትሕ የሚባሉት እሴቶች ይማርኩኝ ነበር፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ የፍትሕ መጓደልና ምግባረ ብልሹነት ሳይ ግን ተስፋ ቆረጥኩ።
የኮምሶሞል አባል ስለነበርኩ የሶቪየት ኅብረት a መንግሥት ቤተ ክርስቲያኖች እንዲዘጉና ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንዲፈርሱ ያወጣውን አዋጅ የመደገፍ ግዴታ ነበረብኝ። በመንደራችን ውስጥ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ሐቀኛና ሰላማዊ መሆናቸው ትኩረቴን ቢስበውም አክራሪዎች እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር። ለአብዛኞቹ ጥያቄዎቼ ከእነሱ መልስ አገኛለሁ ብዬ ግን ፈጽሞ አላሰብኩም።
በመንደራችን ይኖር የነበረው አጎቴ ዲሚትሪ የይሖዋ ምሥክር ነበር። በ1952 መጀመሪያ አካባቢ አንድ ቀን “ጆርጂ በሕይወትህ ምን ልታደርግ አስበሃል?” ብሎ ጠየቀኝ። ስለ እኔ ከልቡ አስቦ እንዲህ ያለኝ እሱ ብቻ ነበር። እውነቱን ለመናገር፣ መልስ ያላገኘሁላቸው ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ለምሳሌ “አምላክ ካለ፣ ሕይወት እንደዚህ በመከራ የተሞላው ለምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይጉላላ ነበር። በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት ውስጥ ዲሚትሪ ለጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ሰጠኝ። ስለ አምላክ እያወራን እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት የቆየንባቸው ቀናት ነበሩ!
ያደረግነው ውይይት መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ለማጥናት አነሳሳኝ። በጣም የሚወደኝ የሰማይ አባት እንዳለኝ ተገነዘብኩ። (መዝሙር 27:10) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የጠለቀ እውቀት ባይኖረኝም ለይሖዋ ያዳበርኩት ጠንካራ ፍቅር እርምጃ ለመውሰድ አነሳሳኝ። የቡድናችን ሊቀ መንበር ቢዝትብኝም የኮሚኒስት ፓርቲውን ለቅቄ ወጣሁ። መስከረም 1952 ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅሁ፤ ይህ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ ገና አራት ወሬ ነበር።
ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ተፈተነ
በወቅቱ በይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ሆኖም ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር በተግባር ማሳየት ስለፈለግሁ በመንደሮቹ ውስጥ ለሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወንድሞቼ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማድረስ ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። ይህ አደገኛ ነበር፤ ምክንያቱም አንዳንድ የጠረጠሩ ነዋሪዎች ‘ፀጉረ ልውጥ ሰው አየን’ ብለው ለባለሥልጣናቱ ሪፖርት ሊያደርጉ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እንኳ ተጠራጥረውኝ ነበር፤ ጉባኤውን ለመሰለል ሰርገው ከገቡ በርካታ የሚስጥር ፖሊሶች አንዱ እንደሆንኩ አስበው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ሰላይ እንዳልሆንኩ ተረጋገጠ። ከተጠመቅኩ ገና በሁለት ወሬ፣ ‘የታገዱ ጽሑፎች አሰራጭተሃል’ በሚል ተከስሼ በቁጥጥር ሥር ዋልኩ።
ከዚያ በኋላ አንድ ዓመት ገደማ ማረፊያ ቤት ቆየሁ። በዚህ ወቅት ፖሊሶቹ አቋሜን እንዳላላ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ምርመራ ያካሂዱብኝ ነበር። ሆኖም ለይሖዋ ያዳበርኩት ጥልቅ ፍቅር እንዲህ በቀላሉ የሚላላ አልነበረም። በኋላ ላይ ዩክሬን ውስጥ በምትገኘው በኦዴሳ ከተማ ችሎት ፊት እንድቀርብ ተወሰነ። ወላጆቼን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ችሎት ላይ እንዲገኙ ጠሯቸው፤ በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች አልነበሩም።
ችሎት ፊት በቀረብኩበት ወቅት፣ ተታልዬ አደገኛ ኑፋቄን እንደተቀላቀልኩ በመግለጽ ከሰሱኝ። ባለሥልጣናቱ፣ ቤተሰቤ አእምሮዬ ጤነኛ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ለማድረግ ፈልገው ነበር። ወላጆቼ ይህን ሲሰሙ በጣም ደነገጡ። እምነቴን እንድተው እያለቀሱ ጠየቁኝ። እኔ ግን ሳልረበሽ እናቴን እንዲህ አልኳት፦ “አይዞሽ አትጨነቂ። እኔ አልተታለልኩም። ሕይወቴን ሙሉ ስፈልገው የነበረውን ነገር ነው ያገኘሁት፤ መቼም ቢሆን ልተወው አልፈልግም።” (ምሳሌ 23:23) ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ባይኖረኝም ስለ ይሖዋ ያወቅሁት ነገር እሱን የሙጥኝ እንድል አድርጎኝ ነበር። በኋላ ላይ ወላጆቼ ስለ እምነቴ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተዋል፤ በመሆኑም ከስድስት ዓመት ገደማ በኋላ እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ 15 ዓመት ተፈርዶብኝ ወደ ኮሊማ ክልል በባቡር ተላክሁ፤ በሳይቤሪያ በሚገኘው በዚህ ክልል ውስጥ ብዙ የጉልበት ሥራ ካምፖች ነበሩ። የእስር ቤቱ ጠባቂዎችና ፖሊሶች፣ እስረኞቹን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ሲሉ ይደበድቡን እና ያስርቡን ነበር። መጀመሪያ ላይ በሕይወት የምተርፍ አልመሰለኝም ነበር።
አምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ አድርጎልኛል እንዲሁም አሠልጥኖኛል
ካምፑ ከደረስኩ ብዙም ሳይቆይ እዚያ ከነበሩት 34 የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንዶቹ “ቡድናችሁ ውስጥ ኢዮናዳቦች አሉ?” ብለው ጠየቁኝ። መንፈሳዊ ወንድሞቼ እንደሆኑ ወዲያውኑ ገባኝ። እንዲህ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ሊጠቀሙ የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው! እነዚህ የጎለመሱ ወንድሞች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ የማደርገው እንዴት እንደሆነ አስተምረውኛል፤ እንደ ማስተዋል ያሉ መንፈሳዊ ባሕርያትን እንዳዳብርም ረድተውኛል።
ካምፑ ውስጥ ማሽን ላይ እሠራ ነበር። አንድ ቀን ማትፌይ የተባለ የሥራ ባልደረባዬ የ50 ቅዱሳንን ስም በቃሉ እንደሚያውቅ በጉራ ተናገረ። ቅዱሳን ብሎ የጠራቸውን ሰዎች የሚያቃልል ነገር ስናገር ማትፌይ በቡጢ ሊለኝ ተነሳ፤ እኔም ሮጬ አመለጥኩ። በኋላ ላይ ወንድሞች ሲስቁ ሳይ ተበሳጨሁ። “ምን ያስቃችኋል? እኔኮ ልሰብክ ብዬ ነው!” አልኳቸው። ዓላማችን ምሥራቹን መናገር እንጂ ሰዎችን ቅር ማሰኘት እንዳልሆነ በደግነት አስታወሱኝ። (1 ጴጥሮስ 3:15) ማትፌይ የፖለቲካ እስረኛ ነበር፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮቹ ለጠባቂዎቹና ለባለሥልጣናቱ የሚያሳዩት አክብሮት በጣም ያስገርመው ነበር። በኋላ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ። ቀዝቃዛ ውኃ ባለበት በርሜል ውስጥ በሚስጥር የተጠመቀበትን ምሽት መቼም ቢሆን አልረሳውም።
ወደ ካምፑ ከገባን ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔና ሌሎች ሁለት ወጣት ወንድሞች የፖለቲካ ትምህርት የሚሰጥበት ክፍል ውስጥ እንድንገባ ተጋበዝን። መጀመሪያ ላይ፣ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ላይ አንገኝም ብለን ነበር። እንዲህ ማድረግ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን ያስጥሰናል ብለን አስበን ነበር። (ዮሐንስ 17:16) ትምህርቱ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ ባለመሆናችን ለሁለት ሳምንት ጨለማ ክፍል ውስጥ አሰሩን። በኋላ ላይ ስንለቀቅ፣ ወንድሞች እንዲህ ዓይነት ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ብቻ የገለልተኝነት አቋማችንን እንደማያስጥሰን በአሳቢነት አብራሩልን። እንዲያውም አጋጣሚውን ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ልንጠቀምበት እንደምንችል ነገሩን። እነዚህ አፍቃሪ ወንድሞች ሁኔታዎችን በጥበብ እንድንይዝ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተን ውሳኔ የማድረግ ችሎታችንን እንድናሻሽል በደግነት ረድተውናል።
በትዕግሥት የሰጡኝ ሥልጠና ለእኔ የይሖዋ ፍቅርና አሳቢነት መገለጫ ነው። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። እስረኛ የሆነ አንድ ቄስ ዋና የሒሳብ ሠራተኛ እንዲሆን ተሾመ። የምግብ ሰዓት ላይ በተገናኘን ቁጥር “እሺ፣ አንተ የዲያብሎስ ልጅ!” ይለኝ ነበር። አንድ ሌላ እስረኛ “ለምን ‘አቤት አባዬ!’ ብለህ አትመልስለትም?” አለኝ። ክፋቱ፣ ያለኝን አደረግሁ፤ በዚህም የተነሳ ክፉኛ ተደበደብኩ። ወንድሞች የደረሰብኝን ነገር ሲያውቁ ያደረግሁት ነገር ተገቢ እንዳልነበር በደግነት አስረዱኝ። (ምሳሌ 29:11) በኋላ ላይ ቄሱን ይቅርታ ጠየቅሁት።
ወደ ካምፑ ከመላኬ በፊት በምሽት ወይም ንጋት ላይ ጎህ ከመቅደዱ በፊት በድብቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እናደርግ ነበር። ካምፑ ውስጥ ግን በድብቅ ማድረግ የምንችልበት ቦታ አልነበረም። ስለዚህ ጠባቂዎቹ ሊያዩን የሚችሉበት ቦታ ላይ በየቀኑ ከወንድሞች ጋር ክብ ሠርተን እንቆማለን። ከዚያም አስቀድመን በትናንሽ ወረቀቶች ላይ የጻፍናቸውን ጥቅሶች እንወያይባቸዋለን። ዓላማችን በተቻለ መጠን ብዙ ጥቅሶችን በቃላችን ለመያዝ መሞከርና እርስ በርስ መተዋወስ ነው። አንድ ጠባቂ ሲመጣ ካየን ወዲያውኑ ወረቀቱን እንውጠዋለን።
በግዞት ብላክም የአምላክ ፍቅር አልተለየኝም
በ1959 ከካምፑ ከተለቀቅኩ በኋላ በካዛክስታን ወደሚገኘው ካራጋንዳ ክልል በግዞት ተላክሁ። የተጣለብኝ የእንቅስቃሴ ገደብ ባይነሳልኝም ትዳር ለመመሥረት የ20 ቀን ፈቃድ እንዲሰጡኝ ባለሥልጣናቱን ጠየቅኩ። ከዚያም ሩሲያ ውስጥ ወደሚገኘው የቶምስክ ክልል ተጓዝኩ፤ እዚያ ማሪያ የተባለች ታማኝና ደስ የምትል እህት አውቅ ነበር። በባሕርዬ ግልጽ ስለሆንኩ ለማሪያ የመጣሁበትን ጉዳይ በቀጥታ ነገርኳት። “ማሪያ፣ ለመጠናናት ጊዜ የለኝም፤ አግቢኝ!” አልኳት። እሷም እሺ አለች፤ ከዚያም ትንሽ ሠርግ አደረግን። ማሪያን የማረካት በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም ያሳየሁት ጽናት ነው፤ እንዲሁም ከጎኔ ሆና በይሖዋ አገልግሎት ልትደግፈኝ ፈለገች።—ምሳሌ 19:14
በ1960ዎቹ ዓመታት በይፋ ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ማገልገል አንችልም ነበር። ሆኖም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመስበክ ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም ነበር። የሰዎች ቤት ስንጋበዝ ወይም ለሽርሽር ወጣ ስንል፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለን ለሰዎች እንናገራለን። ለመስበክ የሚያስችሉን ሌሎች አጋጣሚዎች ለመፍጠርም ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ፣ ይሸጣሉ ተብሎ ማስታወቂያ ወደወጣባቸው ቤቶች ሄደን ከቤቱ ባለቤቶች ጋር ጨዋታ እንጀምራለን፤ ከዚያም ውይይቱ ወደ መንፈሳዊ ጉዳዮች እንዲያመራ ጥረት እናደርጋለን። እኔና ማሪያ በዚህ መንገድ ጥናት ያስጀመርናቸው ስድስት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
በምርጫ ወቅትም ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ያገኘንበት ጊዜ አለ። አንድ ቀን፣ የተወሰኑ የሚስጥር ፖሊሶች እኔና አንዳንድ ወንድሞች ተቀጥረን ወደምንሠራበት ፋብሪካ መጡ። ፋብሪካው ውስጥ ይሠሩ በነበሩት 1,000 ሠራተኞች ፊት “የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካ ውስጥ የማይገቡት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁን። ዋናው መሐንዲስና ሌሎች በርካታ ሠራተኞች ጥብቅና ቆሙልን። እምነት የሚጣልብን ታታሪ ሠራተኞች እንደሆንን ለፖሊሶቹ ነገሯቸው። እነሱ ያደረጉትን ስናይ አቋማችንን ለማስረዳት ብርታት አገኘን፤ በቃላችን የምናውቃቸውን ጥቅሶች እያነሳን አስረዳናቸው። በድፍረት የሰጠነው ምሥክርነት ልባቸውን ስለነካው አራት ሠራተኞች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ፈለጉ፤ ከዚያም ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ካዛክስታን ውስጥ ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን ተቀብለው ነበር፤ ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ ለማዘጋጀት አሰብን። ሆኖም የባለሥልጣናቱን ትኩረት ሳንስብ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአልማቲ ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ መንደር ከሚደረግ ሠርግ ጋር አያይዘን የአንድ ቀን ስብሰባ ለማድረግ ወሰንን። ዝግጅቱ የተደረገው ለሠርግ ቢሆንም በዚያው ክርስቲያናዊ ስብሰባችንን አደረግን፤ በፕሮግራሙ ላይ ከ300 የሚበልጡ ታዳሚዎች ተገኝተው ነበር! ባለቤቴና የተወሰኑ እህቶች ቦታውን ለማሳመርና ጣፋጭ ምግብ ለማዘጋጀት ብዙ ሠርተዋል። ታዳሚዎቹን ይበልጥ ያስደሰታቸው ግን ተናጋሪዎቹ የሰጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር የሰጠሁት በዚያን ዕለት ነው።
የአምላክ ፍቅር በፈተናዎቻችን ሁሉ ብርታት ሰጥቶናል
ውዷ ባለቤቴ ማሪያ በሕይወት በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ታማኝ አጋር ሆናልኛለች። ለስላሳ ባሕርይ ያላትና ትሑት ሴት ነበረች፤ ምንጊዜም ቅድሚያ የምትሰጠው ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ነበር። ጤናማና ጠንካራ ሴት ብትሆንም ከባድ ደረጃ ላይ ያለ የኦስቲዮፖሮሲስ በሽታ በድንገት አጋጠማት። በዚህም የተነሳ ለ16 ዓመታት ገደማ የአልጋ ቁራኛ ሆናለች። በ2014 ሕይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አስታምመናታል፤ ለዚህም ሊዩድሚላ የተባለችውን ልጃችንን ላመሰግናት እፈልጋለሁ።
ውዷ ባለቤቴ ማሪያ ታምማ በነበረበት ወቅት ተስፋ የምቆርጥባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ሕይወቷ እስካለፈበት ዕለት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ እና የሚያበረታቱ ርዕሶችን አብረን እናነብ ነበር። ብዙ ጊዜ ስለ አዲሱ ዓለም እናወራለን። አንዳንድ ጊዜ ከአጠገቧ ሆኜ ድምፅ ሳላሰማ አለቅሳለሁ። ይሖዋ ስለሰጣቸው አስደናቂ ተስፋዎች ስናነብ ግን ውስጣችን ይረጋጋል፤ ለመጽናት ብርታት እናገኛለን።—መዝሙር 37:18፤ 41:3
ይሖዋ እንደሚወደኝ ከተረዳሁበት ዕለት አንስቶ የእሱ ድጋፍና እንክብካቤ ተለይቶኝ አያውቅም። (መዝሙር 34:19) ወጣት ሳለሁ ተሞክሮ አልነበረኝም፤ ሆኖም ይሖዋ ባሕርዬን እንዳሻሽል በትዕግሥት በረዱኝ ወንድሞች አማካኝነት ፍቅሩን አሳይቶኛል። በጉልበት ሥራ ካምፕና በግዞት ባሳለፍኩት ከባድ ጊዜ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ደግፎኛል። እንዲሁም ውዷ ባለቤቴን ማሪያን እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ ለማስታመም ብርታት ሰጥቶኛል። አዎ፣ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ሕይወቴን በሙሉ ብርታት እንደሆነኝ በልበ ሙሉነት መናገር እችላለሁ።
a እስከ 1991 ድረስ ካዛክስታን፣ ሞልዶቫ እና ዩክሬን የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ክፍል ነበሩ።