በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስትራዝቡርግ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት

ጥቅምት 11, 2024
ስፔን

በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት ለይሖዋ ምሥክሮች የሚፈልጉትን ሕክምና የመምረጥ መብታቸውን አስከበረላቸው

ችሎቱ በከሳሽ ፒንዶ ሙያ እና በተከሳሽ ስፔን መካከል በነበረው ክርክር ላይ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አስተላልፏል

በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት ለይሖዋ ምሥክሮች የሚፈልጉትን ሕክምና የመምረጥ መብታቸውን አስከበረላቸው

መስከረም 17, 2024 በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት፣ ታካሚዎች በሕሊናቸው መሠረት የሚፈልጉትን ሕክምና የመምረጥ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል፤ ችሎቱ ይህን ብይን ያስተላለፈው በሙሉ ድምፅ ነው። ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ይህ ውሳኔ አስገዳጅነቱ በስፔን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት በሆኑት 46 አገራት ውስጥም ጭምር ነው፤ በእነዚህ አገራት ያሉ ታካሚዎች የሚፈልጉትን ሕክምና የመምረጥ መብታቸው እንዲከበርላቸው ያደርጋል።

ሮሳ ፒንዶ ሙያ እና ባለቤቷ አርማንዶ

ሰኔ 2018 የ47 ዓመቷ እህት ሮሳ ፒንዶ ሙያ፣ ቀላል ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በማድሪድ፣ ስፔን ወደሚገኝ ሆስፒታል ገብታ ነበር። ሮሳ ቀዶ ሕክምናውን ከማድረጓ በፊት ለሐኪሞቹ የሕክምና መመሪያ ሰነድ የሰጠቻቸው ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናዋ የተነሳ ደም መውሰድ እንደማትፈልግ በግልጽ አስረድታቸው ነበር። (ሥራ 15:28, 29) የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሮሳ የሰጠችውን መመሪያ የሕክምና መረጃዋ በሚሰፍርበት መዝገብ ላይ ጽፈውት ነበር። ይሁንና ሐኪሞቹ ለሮሳ ከባድ ቀዶ ሕክምና ለማድረግና ደም ለመስጠት ከአንድ ዳኛ ፈቃድ ጠየቁ፤ ዳኛውም ፈቃድ የሰጣቸው ሲሆን ይህ የሆነው ሮሳ ሳታውቅ ነበር። ከቀዶ ጥገናው በኋላ ሮሳ፣ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በግልጽ የሰጠችውን መመሪያ ጥሰው ደም እንደሰጧት ስታውቅ በጣም ደነገጠች።

በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻው ችሎት 17 ዳኞች በከሳሽ ፒንዶ ሙያ እና በተከሳሽ ስፔን ጉዳይ ላይ በሙሉ ድምፅ ባሳለፉት ብይን “ጤናማ አእምሮ ያለውና ለአቅመ አዳም የደረሰ ማንኛውም ታካሚ” የማይፈልገውን የሕክምና ዓይነት “ያለመቀበል መብት” እንዳለው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ችሎቱ እንዲህ ብሏል፦ “የታካሚዎችን አንድን ሕክምና የመቀበል ወይም ያለመቀበል መብት ማክበር ከመሠረታዊ የሕክምና መርሆች አንዱ ነው።”

ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ተደስቷል፤ ይህ ውሳኔ እህት ሮሳ ፒንዶ ሙያ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እምነታቸውንና አመለካከታቸውን መሠረት በማድረግ የሚፈልጉትን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብታቸው እንዲከበርላቸው ያደርጋል።