መስከረም 4, 2023
ቡሩንዲ
የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኪሩንዲ ቋንቋ ወጣ
ነሐሴ 25, 2023 የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኪሩንዲ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መውጣቱ የተነገረው በቡጁምቡራ፣ ቡሩንዲ በተደረገው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተባለው የክልል ስብሰባ ላይ ነው። ፕሮግራሙ በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ባሉ 11 የተለያዩ ቦታዎች ለተሰበሰቡ በአጠቃላይ 15,084 የሚሆኑ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት ተላልፏል። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። ኤሌክትሮኒክ ቅጂውንም ማውረድ ተችሏል።
በቡሩንዲ የሚገኙ የኪሩንዲ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር ወደ 13 ሚሊዮን ይጠጋል። በኪሩንዲ ቋንቋ የሚመራው የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመው በ1969 ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ኪሩንዲ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1985 ነው። በአሁኑ ጊዜ በቡሩንዲ ከ16,900 በላይ ወንድሞችና እህቶች በኪሩንዲ ቋንቋ በሚመሩ 350 ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ። በ2007 ኪሩንዲ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በቋንቋቸው በማግኘታቸው ተደስተው ነበር። አሁን ደግሞ ሙሉውንና የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው በእጅጉ ተደስተዋል።
የይሖዋ ጸጋ በኪሩንዲ ቋንቋ ሲተረጎም “እጅግ የላቀ ደግነት” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል፤ ይህ አገላለጽ በሰጪው ልግስና ላይ የሚያተኩር አገላለጽ ነው። እኛም የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋቸው በማግኘታቸውና የይሖዋን “እጅግ የላቅ ደግነት” በማየታቸው ከተደሰቱት የኪሩንዲ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ከዚህ ደግነት ተጠቃሚ ከሚሆኑ ሁሉ ጋር አብረን እንደሰታለን።—ቲቶ 2:11