በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ጎብኚዎች የ​jw.org ኪዮስክን ሲጎበኙ። ከላይ በስተ ቀኝ፦ ማየትና መስማት የተሳናት አንዲት እህት በዳሰሳ የምልክት ቋንቋ ስትነጋገር። ከታች በስተ ቀኝ፦ jw.org ላይ የሚገኙትን የድምፅ መግለጫዎች ያሏቸውን ቪዲዮዎች የሚያስቃኝ አሳታፊ ስክሪን

ጥቅምት 5, 2022
ብራዚል

የJW.ORGን ተደራሽነት የሚጨምሩ ገጽታዎች በብራዚል ለእይታ ቀረቡ

የJW.ORGን ተደራሽነት የሚጨምሩ ገጽታዎች በብራዚል ለእይታ ቀረቡ

የአካል ጉዳት ማገገሚያ፣ አካታችነትና ተደራሽነት ቴክኖሎጂን የሚያሳይ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል ውስጥ ተካሂዶ ነበር፤ ከመስከረም 1 እስከ 4, 2022 በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሳተፉ ተጋብዘው ነበር። ይህ አውደ ርዕይ ላቲን አሜሪካ ውስጥ የተደራሽነት ቴክኖሎጂ ለእይታ ከሚቀርብባቸው ኤግዚቢሽኖች ትልቁ ነው። የዘንድሮውን ፕሮግራም ከ46,000 የሚበልጡ ሰዎች ተመልክተውታል።

አውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉት ወንድሞችና እህቶች jw.org​ን እንዲሁም JW Library እና JW Library Sign Language የተባሉትን አፕሊኬሽኖች የሚያሳይ ኪዮስክ አዘጋጅተው ነበር። ኪዮስኩ አሳታፊ ስክሪኖች ተገጥመውለታል። ዓይነ ስውርና ማየት የሚቸግራቸው አስፋፊዎችም በቦታው ተገኝተው ድረ ገጻችንና አፕሊኬሽኖቻችን ስላሏቸው የተለያዩ ገጽታዎች ገለጻ አድርገዋል።

የአካል ጉዳት ማገገሚያ ባለሙያ የሆነ አንድ ሰው ኪዮስኩን ከጎበኘ በኋላ እንዲህ ሲል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለማካተት እንዲህ የሚደክም ሃይማኖታዊ ቡድን መኖሩ በጣም አስገራሚ ነው።” ሌላ ጎብኚ ደግሞ “አካታች ከተባለ እንዲህ ነው!” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

የብራዚል ብሔራዊ የዓይነ ስውራን ማኅበር ተወካዮችም በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ተገኝተው ነበር። ተወካዮቹ ከአውደ ርዕዩ ሆነው የሬዲዮ ፕሮግራም አስተላልፈዋል። በአውደ ርዕዩ መክፈቻና መዝጊያ ቀናት፣ ኪዮስኩ ላይ የተሳተፉት ወንድሞች በሬዲዮ ፕሮግራሙ ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። ወንድሞች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያሉ ዓይነ ስውራንን፣ ማየት የሚቸገሩና መስማት የተሳናቸው ሰዎችን እየረዱ እንደሆነ አብራሩ። በአንዱ ቃለ መጠይቅ ላይ አንደኛው የማኅበሩ ተወካይ እንደገለጸው መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ከሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ሁሉ በጣም የወደዳቸው የሚገኙት jw.org ላይ ነው።

ሁለት ወንድሞች በብራዚል ብሔራዊ የዓይነ ስውራን ማኅበር ተወካዮች ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው

ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ሰዎች ልዩ አሳቢነት ያሳያል። (ዘሌዋውያን 19:14) ምሥክሮቹም እሱን በፍቅሩ ሲመስሉት ሲያይ በጣም እንደሚደሰት እርግጠኞች ነን። ‘የዓይነ ስውራን ዓይን የሚገለጥበትንና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮ የሚከፈትበትን’ ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—ኢሳይያስ 35:5