ሰኔ 6, 2024
ኮሎምቢያ
ኮሎምቢያ ውስጥ በተካሄደ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ትኩረት ተሰጠ
ከሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 2, 2024 ቦጎታ፣ ኮሎምቢያ ውስጥ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዷል። አውደ ርዕዩ፣ ከ25 አገራት የመጡ ከ600,000 በላይ ጎብኚዎችን እንዳስተናገደ አዘጋጆቹ ሪፖርት አድርገዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአውደ ርዕዩ ላይ ኪዮስክ ያዘጋጁ ሲሆን ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለት ተዕለት ሕይወት ስለሚሰጠው ጠቃሚ ምክር እና በውስጡ ስላለው የተስፋ መልእክት ግንዛቤ መፍጠር ነው።
ኪዮስካችንን የጎበኘ አንድ ሰው፣ ትንሽ ልጅ ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች የቤተሰቡ ቤት መጥተው አነጋግረዋቸው እንደነበር ገለጸ። አሁንም ስለ አምላክ እና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የመማር ፍላጎት እንዳለው ተናገረ። አንደኛው ወንድማችን፣ ለዘላለም በደስታ ኑር! መጽሐፍን ተጠቅመን አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለምንሰጥበት መንገድ ለሰውየው አስረዳው። ከዚያም ቤቱ አካባቢ የጉባኤ ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታ መፈለግና በjw.org አማካኝነት አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግረው መጠየቅ የሚችልበትን መንገድ አሳየው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ወንድማችን፣ ሰውየው ስልኩ ላይ JW ላይብረሪን ማውረዱን፣ በእሁዱ ስብሰባ ላይ መገኘቱንና በአካባቢው ካለ አንድ ወንድም ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጀመሩን ሲያውቅ በጣም ተደሰተ።
አንዲት ሴት ከትንሽ ልጇ ጋር ወደ ኪዮስካችን መጣች፤ ልጅየው የይሖዋ ወዳጅ ሁን ከተባሉት ቪዲዮዎች አንዱን በደስታ ተመለከተ። እናትየው እንዲህ ያሉ ትምህርታዊ ቪዲዮዎች ከየት መግዛት እንደምትችል አንዷን እህታችንን ጠየቀቻት። እህታችን እነዚህን ቪዲዮዎችም ሆነ ጥሩ ሥነ ምግባርና መንፈሳዊ እሴቶችን ለልጆች የሚያስተምሩ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን jw.org ላይ በነፃ ማግኘት እንደምትችል ለሴትየዋ ነገረቻት። ሴትየዋ ከልጇ ጋር ሌሎች ቪዲዮዎችን ከተመለከተች በኋላ የቪዲዮዎቹን ጥራትና የሚያስተላልፉትን ትምህርት በተመለከተ አድናቆቷን ገለጸች። እህታችን የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚሰጡት አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማየት ትፈልግ እንደሆነ ስትጠይቃት ሴትየዋ ግብዣውን በደስታ ተቀበለች፤ ውይይቱን ለመቀጠልም በቀጠሮ ተለያይተዋል።
የኮሎምቢያ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሰዎች “በይሖዋ ብርሃን [እንዲሄዱ]” ለመርዳት የሚያስችል እንዲህ ያለ ግሩም አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስተናል።—ኢሳይያስ 2:5