በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 12, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ በሩዋንዳና በዚምባብዌ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የምግብ እርዳታ አገኙ

በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ በሩዋንዳና በዚምባብዌ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የምግብ እርዳታ አገኙ

የሩዋንዳና የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በየአካባቢው ካሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለኢኮኖሚ ችግር ለተዳረጉ ወንድሞችና እህቶች መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ጥረት እያደረጉ ነው።

ሩዋንዳ

ሚያዝያ 2, 2020 ላይ የሩዋንዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ፣ በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞችና እህቶች መኖራቸውን እንዲያጣሩና እርዳታ እንዲሰጡ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለጉባኤ ሽማግሌዎች ልኮ ነበር። በመሆኑም በመላው አገሪቱ ያሉ ሽማግሌዎች ይህን ካጣሩ በኋላ ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን መስጠት ጀመሩ።

እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሩዋንዳ ቅርንጫፍ ቢሮ 31 የሚያህሉ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ኮሚቴዎቹ እንደ በቆሎ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ባቄላ፣ ጨው፣ ስኳርና የምግብ ዘይት የመሳሰሉ ነገሮችን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች አከፋፍለዋል። እስካሁን ድረስ ከ7,000 የሚበልጡ ቤተሰቦች እርዳታ ተደርጎላቸዋል።

እህት ኒዜዪማና ሻርሎትና ሦስት ልጆቿ የምግብ እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ እንዲህ በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፦ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ ከባድ ጊዜ በመንፈሳዊም ሆነ በቁሳዊ ለምታደርጉልን የማይቋረጥ እርዳታ በጣም እናመሰግናለን። አድናቆታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል።”

አንድ ወንድም ለቤተሰቡ የምግብ እርዳታ መውሰድ እንደሚችል በተነገረው ዕለት የነበረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “በዚያን ቀን ባለቤቴ በረሃብ ምክንያት ራሷን ስታ ነበር። በድንገት አንድ ወንድም ደውሎ ለእኔና ለቤተሰቤ የሚሆን ምግብ እንድወስድ ነገረኝ። ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ነበር። ሌሊቱን ሙሉ ይሖዋን ሳመሰግን አደርኩ።”

ዚምባብዌ

በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገሪቱ ቀድሞውንም የነበረውን የምግብ እጥረት ይበልጥ አባብሶታል።

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱ የሚደረገውን የእርዳታ ሥራ እንዲያስተባብሩ አምስት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው አስፋፊዎች ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞችና እህቶች ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን መለገስ የሚችሉበት ዝግጅት አድርጓል። ኮሚቴዎቹ በእርዳታ የተገኙትን ቁሳቁሶች እያከፋፈሉ ነው።

የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ እስካሁን ድረስ 62,669 ኪሎ ግራም የበቆሎ ዱቄት፣ 6,269 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 3,337 ኪሎ ግራም የደረቀ ዓሣ (ካፔንታ) እንዲሁም 5,139 ኪሎ ግራም ባቄላ ለ7,319 አስፋፊዎች አከፋፍለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ምግብ አጥተው ተቸግረው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናቸው ወንድም ምግብ ይዞላቸው ሲሄድ ልባቸው በጥልቅ ተነካ። ወንድም ምግብ ይዞላቸው ከመሄዱ በፊት በነበረው ዕለት ቀድሞ የነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ደውሎላቸው ነበር። ፓስተሩ የደወለው እሱና ባለቤቱ የሚያስፈልጓቸውን አንዳንድ ነገሮች መግዛት እንዲችሉ ገንዘብ እንዲሰጡት ለመጠየቅ ነበር። ባልና ሚስቱ በፓስተሩና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ሲመለከቱ ከቤተ ክርስቲያኑ መልቀቃቸውን በይፋ ለማሳወቅ ወሰኑ።

ይሖዋ ይህን የእርዳታ አገልግሎት በመባረክ በሩዋንዳና በዚምባብዌ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ እንደሚያደርግ እንተማመናለን።—የሐዋርያት ሥራ 11:29