በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥራት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥራት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የጥንቶቹ እስራኤላውያን እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ሲሉ ከዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አሥራት a ወይም አንድ አሥረኛውን እንዲሰጡ ታዘው ነበር። አምላክ “በየዓመቱ ከእርሻህ ላይ ከምታገኘው ምርት ሁሉ አንድ አሥረኛውን [“አሥራት” የ1954 ትርጉም] መስጠት አለብህ” በማለት አዟቸው ነበር።—ዘዳግም 14:22

 አሥራት አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው የሙሴ ሕግ አንዱ ክፍል ነበር። ሆኖም ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ አሥራት የመስጠት ግዴታ የለባቸውም። (ቆላስይስ 2:13, 14) ከዚህ ይልቅ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ [ክርስቲያን] ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን” የገንዘብ መዋጮ መስጠት ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 9:7

 አሥራት እና መጽሐፍ ቅዱስ—“ብሉይ ኪዳን”

 በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ አሥራት ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። አሥራት በብዛት የተጠቀሰው የሙሴ ሕግ ለእስራኤል ብሔር በሙሴ አማካኝነት ከተሰጠ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ይሁንና አሥራት ከሙሴ ሕግ በፊትም የተጠቀሰባቸው አንዳንድ ቦታዎች አሉ።

ከሙሴ ሕግ በፊት

 አሥራት እንደሰጠ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው አብራም (አብርሃም) ነበር። (ዘፍጥረት 14:18-20፤ ዕብራውያን 7:4) አብራም ለሳሌም ንጉሣዊ ካህን አሥራት ወይም ስጦታ የሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምም ሆነ ልጆቹ ከዚያ በኋላ አሥራት እንደሰጡ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የለም።

 አሥራት እንደሰጠ የተጠቀሰው ሁለተኛው ሰው ደግሞ የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ነው። ያዕቆብ አምላክ ከባረከው፣ ከሚያገኘው “ከማንኛውም ነገር አንድ አሥረኛውን” ለአምላክ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 28:20-22) ያዕቆብ ይህን አሥራት የሰጠው የእንስሳት መሥዋዕት በማቅረብ እንደሆነ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይናገራሉ። ያዕቆብ አሥራቱን በመስጠት መሐላውን የጠበቀ ቢሆንም የቤተሰቡ አባላት ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ አላስገደዳቸውም።

በሙሴ ሕግ ሥር

 የጥንቶቹ እስራኤላውያን አሥራት በመስጠት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲደግፉ ታዘው ነበር።

  •   ሕዝቡ የሚሰጠው አሥራት እንደ ሌዋውያንና ካህናት ያሉ የሚያለሙት መሬት የሌላቸውን የሙሉ ጊዜ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ለመደገፍ ይውላል። (ዘኁልቁ 18:20, 21) በክህነት የማያገለግሉት ሌዋውያን ከሕዝቡ ከተቀበሉት አሥራት ላይ ምርጥ የሆነውን “የአንድ አሥረኛውን አንድ አሥረኛ” ለካህናቱ ይሰጡ ነበር።—ዘኁልቁ 18:26-29

  •   ሕዝቡ ሁለተኛ ዓመታዊ አሥራት መስጠትም ይጠበቅባቸው የነበረ ይመስላል፤ ሌዋውያንም ሆኑ ሌዋዊ ያልሆኑ ሰዎች ከዚህ አሥራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። (ዘዳግም 14:22, 23) እስራኤላውያን ቤተሰቦች ሁለተኛውን አሥራት የሚሰጡት በልዩ በዓላት ወቅት ነበር፤ በየተወሰነ ዓመት ደግሞ አሥራቱ በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎችን ለመንከባከብ ይውላል።—ዘዳግም 14:28, 29፤ 26:12

 አሥራት የሚሰላው እንዴት ነበር? እስራኤላውያን በየዓመቱ ከእርሻቸው ምርት አንድ አሥረኛውን ለይተው ያስቀምጡ ነበር። (ዘሌዋውያን 27:30) ይህን አሥራት በምርት ሳይሆን በገንዘብ ለመክፈል ከመረጡ ተጨማሪ 20 በመቶ መስጠት ይኖርባቸዋል። (ዘሌዋውያን 27:31) “ከከብቶቹና ከመንጋው መካከል አንድ አሥረኛ” እንዲሰጡም ታዘው ነበር።—ዘሌዋውያን 27:32

 የከብቶች አሥራትን ለመወሰን አስራኤላውያን ከበረታቸው የሚወጣውን እያንዳንዱን አሥረኛ እንስሳ መለየት ነበረባቸው። ሕጉ ለዚህ ዓላማ የተለዩትን እንስሳት መመርመርም ሆነ መለወጥ እንዲሁም የከብቶችን አሥራት በገንዘብ መክፈል አይፈቅድም ነበር። (ዘሌዋውያን 27:32, 33) ለዓመታዊ በዓል የሚሰጡትን ሁለተኛውን አሥራት ግን በገንዘብ መለወጥ ይችሉ ነበር። ይህ ዝግጅት በበዓሉ ላይ ለመገኘት ከሩቅ ቦታ ተጉዘው ለሚመጡ እስራኤላውያን ይበልጥ አመቺ ነበር።—ዘዳግም 14:25, 26

 እስራኤላውያን አሥራት የሚሰጡት መቼ ነበር? እስራኤላውያን በየዓመቱ አሥራት ይሰጡ ነበር። (ዘዳግም 14:22) ሆኖም በሰባተኛው ዓመት የተለየ ነገር ያደርጉ ነበር። ሰባተኛው ዓመት ሰንበት ወይም የእረፍት ዓመት በመሆኑ እስራኤላውያን በዚያ ዓመት እህል አይዘሩም። (ዘሌዋውያን 25:4, 5) በዚህ ለየት ያለ ሁኔታ የተነሳ በዚያ ዓመት የመከር ወቅት ላይ አሥራት አይሰበሰብም። ከሰባተኛው ዓመት በኋላ ባለው ሦስተኛና ስድስተኛ ዓመት ላይ እስራኤላውያን ሁለተኛውን አሥራት ለድሆችና ለሌዋውያን ያካፍሉ ነበር።—ዘዳግም 14:28, 29

 አሥራት ያልሰጠ ሰው ምን ይቀጣ ነበር? የሙሴ ሕግ አሥራት አለመስጠት ቅጣት እንዳለው አይናገርም። አሥራት መስጠት የሕሊና ግዴታ ነው። እስራኤላውያን አሥራት ከሰጡ በኋላ አሥራት መስጠታቸውን ለአምላክ በመግለጽ እንዲባርካቸው ይለምኑ ነበር። (ዘዳግም 26:12-15) አምላክ አሥራት አለመስጠትን ከእሱ እንደመስረቅ ይቆጥረው ነበር።—ሚልክያስ 3:8, 9

 አሥራት መስጠት ከባድ ሸክም ነበር? በፍጹም። አምላክ እስራኤላውያን አሥራት ከሰጡ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስላቸውና የሚጎድልባቸው ነገር እንደማይኖር ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ሚልክያስ 3:10) በሌላ በኩል ደግሞ አሥራት በማይሰጡበት ጊዜ ችግር ይደርስባቸው ነበር። የአምላክን በረከት የሚያጡ ከመሆኑም ሌላ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ችላ በማለታቸው እነሱ ከሚያቀርቡት አገልግሎት መጠቀም አይችሉም ነበር።—ነህምያ 13:10፤ ሚልክያስ 3:7

 አሥራት እና መጽሐፍ ቅዱስ—“አዲስ ኪዳን”

 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ በኖረበት ወቅትም የአምላክ አገልጋዮች አሥራት መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ግን ይህ ሥርዓት አቆመ።

በኢየሱስ ዘመን

 በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባል የሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እስራኤላውያን አሥራት መስጠታቸውን ቀጥለው እንደነበር ይገልጻል። ኢየሱስ እስራኤላውያን አሥራት መስጠትን ችላ ማለት እንደሌለባቸው ተናግሯል፤ ያም ቢሆን የሚጠበቅባቸውን አሥራት በሙሉ እየሰጡ “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ” የሚሉትን የሃይማኖት መሪዎች አውግዟል።—ማቴዎስ 23:23

ከኢየሱስ ሞት በኋላ

 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ የአሥራት ሕግ ተሻረ። የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ‘አሥራት የመሰብሰብን ትእዛዝ’ ጨምሮ የሙሴን ሕግ ሽሯል ወይም አስወግዷል።—ዕብራውያን 7:5, 18፤ ኤፌሶን 2:13-15፤ ቆላስይስ 2:13, 14

a አሥራት “አንድ ሰው ለሆነ ዓላማ ሲል ለይቶ የሚያስቀምጠው የገቢው አንድ አሥረኛ ነው። . . . አሥራት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በአብዛኛው የተሠራበት ለሃይማኖታዊ ዓላማ የተሰጠን መዋጮ ለማመልከት ነው።”—ሃርፐርስ ባይብል ዲክሽነሪ ገጽ 765