መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አይጋጭም፤ መላው መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይስማማል። እርግጥ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦች ይኖሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ከታች የተጠቀሱትን ነጥቦች ግምት ውስጥ በማስገባት የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦችን በትክክል መረዳት ይቻላል።
ዐውዱን መመልከት። የትኛውም መጽሐፍ ላይ ቢሆን የአንድን ሐሳብ ዐውድ ግምት ውስጥ ካላስገባን ጸሐፊው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ነገሮችን እንዳሰፈረ ልንደመድም እንችላለን።
የጸሐፊውን እይታ ግምት ውስጥ ማስገባት። የአንድ ክንውን የዓይን ምሥክሮች ትክክለኛ መረጃ ቢሰጡም ስለ ክንውኑ ሲተርኩ የተለያዩ ቃላት ሊጠቀሙ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ስለ ክንውኑ የሚጠቅሷቸው ዝርዝር ጉዳዮች ይለያዩ ይሆናል።
የታሪክ ማስረጃዎችንና በወቅቱ የነበሩ ልማዶችን ግምት ውስጥ ማስገባት።
አንድ ቃል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል በቃል ይሁን በዘይቤያዊ አነጋገር ማረጋገጥ።
አንድ ሰው አንድን ድርጊት ራሱ ባይፈጽመውም እንኳ እሱ እንደፈጸመው ተደርጎ ሊገለጽ እንደሚችል ማሰብ። a
ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መጠቀም።
የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ወይም አመለካከቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማስማማት አለመሞከር።
እነዚህን ነጥቦች ግምት ውስጥ በማስገባት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦችን በትክክል መረዳት እንደሚቻል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
ነጥብ 1፦ ዐውድ
አምላክ በሰባተኛው ቀን ካረፈ መሥራቱን እንደቀጠለ የተገለጸው ለምንድን ነው? ዐውዱን ማለትም ስለ ፍጥረት የሚናገረውን የዘፍጥረት ዘገባ መመልከት እንችላለን፤ “ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ” ሲል አምላክ ከምድር ጋር በተያያዘ የሚያከናውነውን የፍጥረት ሥራ ማመልከቱ ነው። (ዘፍጥረት 2:2-4) ኢየሱስ ስለ አምላክ ሲናገር “እስካሁን እየሠራ ነው” ማለቱ ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው አምላክ ስለሚያከናውናቸው ሌሎች ሥራዎች ነው። (ዮሐንስ 5:17) ከእነዚህ ሥራዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስን ማስጻፉ እንዲሁም የሰውን ዘር ለመምራትና ለማዳን ያከናወናቸው ነገሮች ይገኙበታል።—መዝሙር 20:6፤ 105:5፤ 2 ጴጥሮስ 1:21
ነጥብ 2 እና 3፦ የጸሐፊው እይታ እና ታሪክ
ኢየሱስ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው የፈወሰው የት ነው? የሉቃስ መጽሐፍ ኢየሱስ “ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ” ዓይነ ስውር ሰው እንደፈወሰ ይገልጻል፤ ማቴዎስ ደግሞ ይህንኑ ታሪክ ሲዘግብ ኢየሱስ “ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ” ሳለ ሁለት ዓይነ ስውሮች እንዳጋጠሙት ይናገራል። (ሉቃስ 18:35-43፤ ማቴዎስ 20:29-34) ታሪኩን ከሁለት የተለያየ እይታ አንጻር የተመለከቱት ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው እነዚህ ሁለት ዘገባዎች አንዳቸው በሌላው ላይ ያልተጠቀሰ ዝርዝር ሐሳብ አካትተዋል። ማቴዎስ በዓይነ ስውሮቹ ቁጥር ላይ በማተኮር ሁለት እንደሆኑ ሲገልጽ ሉቃስ ደግሞ ኢየሱስ ባነጋገረው አንደኛው ዓይነ ስውር ላይ ትኩረት አድርጓል። ቦታውን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እንደደረሱበት ከሆነ በኢየሱስ ዘመን ኢያሪኮ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ከተሞች ነበሩ፤ ጥንታዊ የሆነው አንደኛው ከተማ የአይሁዳውያን ከተማ ሲሆን ያን ያህል ጥንታዊ ካልሆነው የሮማውያን ከተማ 1.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ይገኝ ነበር። ኢየሱስ ተአምሩን የፈጸመው በእነዚህ ሁለት ከተሞች መካከል ሳለ ሊሆን ይችላል።
ነጥብ 4፦ ዘይቤያዊ አገላለጽ
ምድር ትጠፋለች? መክብብ 1:4 “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” በማለት ይናገራል፤ አንዳንዶች ይህ ሐሳብ “ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል” ከሚለው ጥቅስ ጋር እንደሚጋጭ ይሰማቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:10 አ.መ.ት) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ምድር” የሚለው ቃል ፕላኔታችንን ለማመልከት ቢሠራበትም በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችንም ለማመልከት ዘይቤያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። (ዘፍጥረት 1:1፤ 11:1 የ1954 ትርጉም) በ2 ጴጥሮስ 3:10 ላይ “ምድር” እንደምትቃጠል መገለጹ ፕላኔታችን እንደምትጠፋ ሳይሆን “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች [እንደሚጠፉ]” የሚያመለክት ነው።—2 ጴጥሮስ 3:7
ነጥብ 5፦ በዋነኝነት ሥራውን ያከናወነው ሰው
ኢየሱስ በቅፍርናሆም በነበረበት ወቅት ቀርቦ ያነጋገረው ማን ነው? ማቴዎስ 8:5, 6 የመቶ አለቃው ራሱ ኢየሱስን ቀርቦ እንዳነጋገረው ይገልጻል፤ ሉቃስ 7:3 ግን የመቶ አለቃው የአይሁድ ሽማግሌዎችን ልኮ ልመናውን እንዳቀረበ ይናገራል። እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የሚጋጩ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ሆኖም በዋነኝነት ልመናውን ያቀረበው የመቶ አለቃው እንደሆነ፣ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ግን አማላጅ አድርጎ ወደ ኢየሱስ እንደላካቸው ስንመለከት ሐሳቡ ግልጽ ይሆንልናል።
ነጥብ 6፦ ትክክለኛ ትርጉም
ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን? ሁላችንም ኃጢአትን ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም እንደወረስን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ሮም 5:12) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጥሩ ሰው “ኀጢአትን አያደርግም” ወይም “ኃጢአት አይሠራም” በማለት ከዚህ እውነታ ጋር የሚጋጭ የሚመስል ሐሳብ አስፍረዋል። (1 ዮሐንስ 3:6 አ.መ.ት፣ የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ 1 ዮሐንስ 3:6ን መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ብንመለከተው በጥቅሱ ላይ የገባው “ኃጢአት” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው በተደጋጋሚ የሚደረግ ነገርን ነው። ከአዳም በወረስነው ልናመልጠው በማንችለው ኃጢአትና ሆን ብሎ የአምላክን ሕጎች በተደጋጋሚ በመጣስ በሚደረግ ኃጢአት መካከል ልዩነት አለ። በመሆኑም አንዳንድ ትርጉሞች፣ ይህን ሐሳብ “ኃጢአት መሥራትን ልማድ አያደርግም” በማለት በትክክል ያስቀመጡት ሲሆን ይህም የሚጋጭ የሚመስለውን ሐሳብ ለመረዳት ያስችለናል።—አዲስ ዓለም ትርጉም
ነጥብ 7፦ የሐሰት ትምህርቶችን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን መከተል
ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነው ወይስ ከእሱ ያንሳል? ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት የተናገረው ሐሳብ በሌላ ወቅት “አብ ከእኔ ይበልጣል” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ይመስላል። (ዮሐንስ 10:30፤ 14:28) እነዚህን ጥቅሶች በትክክል ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚል መመርመር አለብን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅሱ መጽሐፍ ቅዱስ የማያስተምረውን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንዲደግፍልን ለማድረግ መሞከር የለብንም። ይሖዋ፣ የኢየሱስ አባት ብቻ ሳይሆን አምላክም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል፤ በመሆኑም ኢየሱስም እንኳ ይሖዋን ያመልካል። (ማቴዎስ 4:10፤ ማርቆስ 15:34፤ ዮሐንስ 17:3፤ 20:17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3) ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል አይደለም።
“እኔና አብ አንድ ነን” የሚለውን ጥቅስ ዐውድ ስንመለከት ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው የዓላማ አንድነትን በተመለከተ ሲሆን እሱና አባቱ ይሖዋ አምላክ አንድ ዓይነት ዓላማ እንዳላቸው መግለጹ ነበር። ኢየሱስ በመቀጠል “አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለውና እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:38) ኢየሱስ ከተከታዮቹም ጋር በዓላማ አንድ እንደሆነ ገልጿል፤ ተከታዮቹን አስመልክቶ ለአምላክ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት አለኝ፣ አንተም ከእኔ ጋር አንድነት አለህ።”—ዮሐንስ 17:22, 23
a ለምሳሌ ያህል፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ታጅ ማሃል “የተገነባው የሙጋል ንጉሠ ነገሥት በሆነው በሻህ ጃሀን” እንደሆነ ይናገራል። ይሁን እንጂ ግንባታውን ያከናወነው እሱ ራሱ አልነበረም፤ ምክንያቱም ኢንሳይክሎፒዲያው አክሎ እንደሚገልጸው “ከ20,000 የሚበልጡ ሠራተኞች ተቀጥረው” ግንባታውን አከናውነዋል።