“ሰብአ ሰገል” እነማን ነበሩ? “ኮከቡን” ያዘጋጀው አምላክ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ብዙዎች ኢየሱስ ሲወለድ “ሰብአ ሰገል” ወይም “ሦስት ጠቢባን” እሱን ለማየት እንደሄዱ ያምናሉ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “ሦስቱ ጠቢባን” ወይም “ሦስቱ ነገሥታት” በማለት አይጠራቸውም። (ማቴዎስ 2:1) የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ ኢየሱስን ለማየት የሄዱትን ሰዎች ለመግለጽ ማዪ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። ይህ ቃል በኮከብ ቆጠራና በጥንቆላ የተካኑ ሰዎችን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። a በመሆኑም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን ሰዎች “ኮከብ ቆጣሪዎች” ወይም “የከዋክብት ተመራማሪዎች” ብለው ይጠሯቸዋል። b
“ሰብአ ሰገል” ስንት ነበሩ?
መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ አይናገርም፤ እንዲሁም ሰዎች ቁጥራቸውን አስመልክቶ የተለያየ አመለካከት አላቸው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ከሆነ “ምሥራቃውያን ሰብአ ሰገል ቁጥራቸው 12 እንደሆነ ያምናሉ፤ ምዕራባውያን ደግሞ ሰብአ ሰገል ሦስት እንደሆኑ ያምናሉ። ምዕራባውያን እንዲህ ያለ አመለካከት የያዙት ሰብአ ሰገል ለሕፃኑ ሦስት ስጦታ ይኸውም ‘ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ’ (ማቴዎስ 2:11) ይዘው በመምጣታቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።”
“ሰብአ ሰገል” ነገሥታት ነበሩ?
ከገና በዓል ጋር በተያያዘ በሚነገሩ ታሪኮች ላይ ሰብአ ሰገል ነገሥታት እንደሆኑ ቢገለጽም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች ነገሥታት እንደሆኑ አይናገርም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚናገረው ከሆነ ኢየሱስ ከተወለደ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ልደት በሚገልጸው ታሪክ ላይ አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችን በመጨመር ሰብአ ሰገል ነገሥታት እንደሆኑ ይናገሩ ጀመር።
“ሰብአ ሰገል” ስማቸው ማን ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ የኮከብ ቆጣሪዎቹን ስም አይናገርም። ኢንተርናሽናል ስታንዳንርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው “ስማቸው (ለምሳሌ ጋስፓር፣ ሜልክዮርና ባልታዛር) የመጣው ከአፈ ታሪኮች ነው።”
“ሰብአ ሰገል” ኢየሱስን ለማየት የሄዱት መቼ ነበር?
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ለማየት የሄዱት ከተወለደ ከበርካታ ወራት በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስን ለመግደል ይፈልግ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ሕፃናት እንዲገደሉ ማዘዙ ይህን ያረጋግጣል። ሄሮድስ በዚያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሕፃናት ላይ እርምጃ የወሰደው ከኮከብ ቆጣሪዎቹ ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ነው።—ማቴዎስ 2:16
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ሊያዩት የሄዱት በተወለደበት ቀን አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ቤት ሲገቡም ልጁን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት” ይላል። (ማቴዎስ 2:11) ይህ ዘገባ የኢየሱስ ቤተሰብ በዚያ ወቅት ይኖር የነበረው ቤት ውስጥ እንደሆነና ኢየሱስም በግርግም ውስጥ የተኛ ሕፃን እንዳልነበረ በግልጽ ያሳያል።—ሉቃስ 2:16
“ሰብአ ሰገል” “ኮከቡን” እንዲከተሉ ያደረገው አምላክ ነው?
አንዳንድ ሰዎች ኮከብ ቆጣሪዎቹን ወደ ኢየሱስ የመራቸውን “ኮከብ” ያዘጋጀው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁንና ይህ አመለካከት ስህተት የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት።
“ኮከቡ” ሰብአ ሰገልን መጀመሪያ የመራቸው ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ‘የተወለደው የአይሁዳውያን ንጉሥ የሚገኘው የት ነው? በምሥራቅ ሳለን ኮከቡን በማየታችን ልንሰግድለት መጥተናል’ አሉ።”—ማቴዎስ 2:1, 2
ሰብአ ሰገልን በመጀመሪያ ወደ ቤተልሔም የመራቸው “ኮከቡ” ሳይሆን ንጉሥ ሄሮድስ ነበር። ሄሮድስ እሱን የሚቀናቀን “የአይሁዳውያን ንጉሥ” እንደሚመጣ ሲሰማ ተስፋ የተደረገበት ክርስቶስ የት እንደሚወለድ አጣራ። (ማቴዎስ 2:3-6) መሲሑ የሚወለደው በቤተልሔም እንደሆነ ሲያውቅ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወደ ቤቴልሔም ሄደው ሕፃኑን እንዲፈልጉና ያለበትን እንዲነግሩት ላካቸው።
ከዚያም ኮከብ ቆጣሪዎቹ ወደ ቤቴልሔም ሄዱ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እነሱም ንጉሡ የነገራቸውን ከሰሙ በኋላ ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ እነሆም፣ በምሥራቅ ሳሉ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ቦታ እስከቆመበት ጊዜ ድረስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር።”—ማቴዎስ 2:9
“ኮከቡ” መታየቱ የኢየሱስን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ ከመሆኑም ሌላ ምንም የማያውቁ ሕፃናት እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል። ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከቤቴልሔም ሲወጡ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ አምላክ አስጠነቀቃቸው።—ማቴዎስ 2:12
ታዲያ ሄሮድስ ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹ እንዳታለሉት ሲያውቅ በጣም ተናደደ፤ ኮከቡ የታየበትን ጊዜ በተመለከተ ከኮከብ ቆጣሪዎቹ ባገኘው መረጃ መሠረት ሰዎች ልኮ በቤተልሔምና በአካባቢዋ ሁሉ የሚገኙትን ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑትን ወንዶች ልጆች በሙሉ አስገደለ።” (ማቴዎስ 2:16) አምላክ እንዲህ ያለ ክፉ ነገር እንዲፈጸም እንደማያደርግ የታወቀ ነው።—ኢዮብ 34:10