ኔፍሊሞች እነማን ናቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ኔፍሊሞች በኖኅ ዘመን ሥጋ የለበሱ ክፉ መላእክት ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር በፈጸሙት የፆታ ግንኙነት የተወለዱ ዲቃላዎች ሲሆኑ ጨካኞችና ጉልበተኞች ነበሩ። a
መጽሐፍ ቅዱስ “የእውነተኛው አምላክ ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:2) በዚህ ጥቅስ ላይ ‘የአምላክ ልጆች’ የተባሉት መንፈሳዊ ፍጥረታት ሲሆኑ በሰማይ ያለውን “ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን” በመተው እንዲሁም የሰው አካል በመልበስ “የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው” በመውሰድ በአምላክ ላይ ዓምፀዋል።—ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:2
ከተፈጥሮ ውጪ የተወለዱት እነዚህ ዲቃላዎች ተራ ሰዎች አልነበሩም። (ዘፍጥረት 6:4) ኔፍሊሞች ግዙፍ እና ጨካኝ የነበሩ ሲሆን ምድር በዓመፅ እንድትሞላ አድርገው ነበር። (ዘፍጥረት 6:13) መጽሐፍ ቅዱስ ኔፍሊሞች “በጥንት ዘመን በኃያልነታቸው ዝና ያተረፉ ሰዎች” እንደነበሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:4) የፈጸሙት ዓመፅና የነበራቸው አስፈሪነት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ትቶ አልፏል።— ዘፍጥረት 6:5፤ ዘኁልቁ 13:33 b
ብዙዎች ኔፍሊሞችን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ ኔፍሊሞች አሁን ድረስ በምድር ላይ አሉ።
እውነታው፦ ይሖዋ ጥንት የነበረውን ዓመፀኛ ዓለም በጥፋት ውኃ አጥፍቷል። ኔፍሊሞችም ሆኑ ሌሎቹ ዓመፀኛ ሰዎች ተጠራርገው ጠፍተዋል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ኖኅ እና ቤተሰቡ የይሖዋን ሞገስ በማግኘታቸው እነሱ ብቻ ከጥፋቱ መትረፍ ችለዋል።—ዘፍጥረት 6:9፤ 7:12, 13, 23፤ 2 ጴጥሮስ 2:5
የተሳሳተ አመለካከት፦ የኔፍሊሞች አባቶች ሰዎች ናቸው።
እውነታው፦ የኔፍሊሞች አባቶች፣ “የእውነተኛው አምላክ ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል። (ዘፍጥረት 6:2) መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን ለማመልከት ተመሳሳይ አባባል ይጠቀማል። (ኢዮብ 1:6፤ 2:1፤ 38:7) መላእክት የሰው አካል የመልበስ ችሎታ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 19:1-5፤ ኢያሱ 5:13-15) ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በእስር ላሉ መናፍስት ማለትም በኖኅ ዘመን አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ ለቀሩት መናፍስት እንደተሰበከላቸው’ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:19, 20) መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ይሁዳም ይህንኑ ሁኔታ አስመልክቶ ሲጽፍ፣ ‘መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁና ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን የተዉ’ አንዳንድ መላእክት መኖራቸውን ጠቅሷል።—ይሁዳ 6
የተሳሳተ አመለካከት፦ ኔፍሊሞች ከሰማይ የተባረሩ መላእክት ናቸው።
እውነታው፦ በዘፍጥረት 6:4 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ኔፍሊሞች፣ የሰው አካል በለበሱ መላእክት እና በሰዎች ሴቶች ልጆች መካከል በተፈጸመ የፆታ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች እንጂ መላእክት አይደሉም። መላእክቱ “የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው መውሰድ” ከጀመሩ በኋላ ይሖዋ በ120 ዓመት ውስጥ አምላካዊ ፍርሃት የሌለውን ይህንን ዓለም እንደሚያጠፋው ተናግሯል። (ዘፍጥረት 6:1-3) ዘገባው ሲቀጥል “በዚያ ጊዜም የእውነተኛው አምላክ ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ግንኙነት ፈጸሙ” ይላል፤ በውጤቱ ደግሞ ‘በጥንት ዘመን ኃያል’ የነበሩት ኔፍሊሞች ሊወለዱ ችለዋል።—ዘፍጥረት 6:4
a “ኔፍሊም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “የሚያፈርጡ” ይኸውም ሌሎችን እያነሱ የሚያፈርጡ ማለት ሳይሆን አይቀርም። ዊንሰንስ ኦልድ ቴስታመንት ወርድ ስተዲስ የተባለው መጽሐፍ ይህ ቃል “ሰዎችን የሚያጠቁና የሚዘርፉ እንዲሁም ሌሎች እንዲወድቁ የሚያደርጉ” ሰዎችን እንደሚያመለክት ገልጿል።
b በዘኁልቁ 13:33 ላይ የተጠቀሱት የእስራኤል ሰላዮች የተመለከቷቸው ሰዎች ቁመና፣ ከመቶ ዓመታት በፊት ስለሞቱት ኔፊሊሞች እንዲያስታውሱ እንዳደረጋቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።—ዘፍጥረት 7:21-23