መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው ከሥቃይ ለመገላገል ሲባል እንዲሞት ማድረግን በተመለከተ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው ከሥቃዩ ለመገላገል ሲባል እንዲሞት a ማድረግን አስመልክቶ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ስለ ሕይወትና ስለ ሞት የሚናገረው ነገር ስለዚህ ጉዳይ ትክክለኛ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን ማጥፋት በምንም መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው ይናገራል፤ ሆኖም አንድ ሰው ፈጽሞ ሊድን እንደማይችል ከተረጋገጠ ሕይወቱን ለማራዘም ማንኛውንም መሥዋዕት መክፈል እንዳለብን አይናገርም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የሰው ልጆች ፈጣሪና “የሕይወት ምንጭ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 36:9፤ የሐዋርያት ሥራ 17:28) በአምላክ ዓይን ሕይወት ውድ ነው። በመሆኑም አምላክ የራስንም ሆነ የሌላን ሰው ሕይወት ማጥፋትን ያወግዛል። (ዘፀአት 20:13፤ 1 ዮሐንስ 3:15) ከዚህም በተጨማሪ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የራሳችንም ሆነ የሌሎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ይናገራል። (ዘዳግም 22:8) ይህም አምላክ ሕይወታችንን እንደ ውድ ስጦታ አድርገን እንድንመለከተው እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው።
ግለሰቡ የማይድን በሽታ ቢይዘውስ?
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው መሞቱ እንደማይቀር ቢታወቅም እንኳ የዚያን ሰው ሕይወት ማጥፋት ትክክል እንደሆነ አይናገርም። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የሳኦል ታሪክ ይህን ያሳያል። ሳኦል በጦርነት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ሊሞት ተቃርቦ በነበረበት ወቅት አገልጋዩን እንዲገድለው ጠይቆት ነበር። (1 ሳሙኤል 31:3, 4) የሳኦል አገልጋይ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ይሁን እንጂ አንድ ሌላ ሰው፣ ሳኦል እንዲገድለው እንደጠየቀውና እሱም እንደገደለው ለዳዊት ነገረው። ዳዊትም ሰውየው ሕይወት በማጥፋቱ ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግሯል። ዳዊት አምላክ ስለ ጉዳዩ ምን አመለካከት እንዳለው በሚገባ የሚያውቅ ሰው ነው።—2 ሳሙኤል 1:6-16
ሕይወት ለማራዘም ማንኛውም መሥዋዕት መከፈል አለበት?
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሊድን እንደማይችል የተረጋገጠ ቢሆንም እንኳ ሕይወቱን ለማራዘም ማንኛውንም መሥዋዕት መክፈል እንዳለብን አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ስለ ጉዳዩ ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ ያበረታታል። ሞት የሰው ልጆች ጠላት ሲሆን ኃጢአተኛ መሆናችን ያስከተለው ውጤት ነው። (ሮም 5:12፤ 1 ቆሮንቶስ 15:26) ማናችንም ብንሆን መሞት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን አምላክ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ ቃል ስለገባልን ሞትን መፍራት አይኖርብንም። (ዮሐንስ 6:39, 40) ለሕይወት አክብሮት ያለው ሰው፣ የተሻለ የሚባለውን ሕክምና ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። ይህ ማለት ግን አንድ ሰው ሁኔታው ምንም ተስፋ እንደሌለው ሙሉ በሙሉ ከተረጋገጠ በኋላም እንኳ የሕክምና መሣሪያ ጥገኛ ሆኖ እስትንፋሱ እንዲቀጥል ጥረት ያደርጋል ማለት አይደለም።
ራስን ማጥፋት ይቅር ሊባል የማይችል ኃጢአት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ራስን ማጥፋት ይቅር ሊባል የማይችል ኃጢአት እንደሆነ አይናገርም። እርግጥ የራስን ሕይወት ማጥፋት ከባድ ኃጢአት መሆኑ አይካድም፤ b ሆኖም አምላክ እንደ አእምሮ ሕመም፣ ከመጠን ያለፈ ውጥረትና በዘር የሚተላለፍ ችግር ያሉ ነገሮች አንድን ሰው ራሱን እንዲያጠፋ ሊገፋፉት እንደሚችሉ በሚገባ ይረዳል። (መዝሙር 103:13, 14) አምላክ ለተጨነቁ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማጽናኛ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይህም ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎችን ጨምሮ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችም ከሞት የመነሳት ተስፋ እንዳላቸው ያሳያል።
a “የምሕረት ግድያ” ወይም አንድ ሰው ከሥቃዩ እንዲገላገል ሲባል እንዲሞት ማድረግ የሚለው አገላለጽ “በጣም የታመመን ወይም ጉዳት የደረሰበትን ሰው ከሥቃዩ ለመገላገል ሲባል መግደልን” ያመለክታል። (ሚርያም ዌብስተር ለርነርስ ዲክሽነሪ) አንድ ሐኪም በታማሚው ጥያቄ መሠረት የበሽተኛው ሕይወት እንዳይቀጥል ሲያደርግ ደግሞ ይህ ድርጊት “በሐኪም እርዳታ ራስን ማጥፋት” (ፊዚሽያን አሲስትድ ሱዊሳይድ) ይባላል።
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ራሳቸውን እንዳጠፉ የተገለጹት ሰዎች ጥቂት ሲሆኑ ሁሉም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረን ነገር ያደረጉ ሰዎች ናቸው።—2 ሳሙኤል 17:23፤ 1 ነገሥት 16:18፤ ማቴዎስ 27:3-5