“ደጉ ሳምራዊ” የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ደጉ ሳምራዊ” የሚለው ስያሜ ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት፣ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን የሚረዳ ሰውን ለማመልከት ነው። ስያሜው የተወሰደው ኢየሱስ ከተናገረው ታሪክ ወይም ምሳሌ ላይ ነው። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ጥሩ ባልንጀራ ዘር፣ ብሔር ሳይል ለሁሉም ሰው ምሕረት እንደሚያሳይና እርዳታ እንደሚሰጥ ለማስተማር ነው።
በዚህ ርዕስ ውስጥ፦
የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ምንድን ነው?
ኢየሱስ የተናገረው ታሪክ በአጭሩ እንዲህ ነው፦ አንድ አይሁዳዊ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ ነበር። መንገድ ላይ ወንበዴዎች አገኙትና ዘረፉት እንዲሁም ደበደቡት፤ ከዚያም በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ሄዱ።
አንድ አይሁዳዊ ካህን፣ በኋላ ላይ ደግሞ ሌላ አይሁዳዊ የሃይማኖት መሪ ሰውየው በወደቀበት ቦታ አለፉ። እነዚህ ሰዎች ከዚህ ሰውዬ ጋር ተመሳሳይ ዘር ቢኖራቸውም አንዳቸውም እሱን ለመርዳት አልቆሙም።
በመጨረሻም ከሌላ ብሔር የሆነ አንድ ሰው በዚያ መንገድ አለፈ። ይህ ሰው ሳምራዊ ነበር። (ሉቃስ 10:33፤ 17:16-18) የወደቀውን ሰው ሲያየው አዘነለትና ቁስሉን ያክምለት ጀመር። ከዚያም ወደ እንግዶች ማረፊያ ወሰደው። ሌሊቱን ሲያስታምመው አደረ። በማግስቱም ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ገንዘብ ሰጠውና ሰውየውን እንዲያስታምምለት ጠየቀው፤ ተጨማሪ ወጪ ካለም ሲመለስ እንደሚከፍለው ነግሮት ሄደ።—ሉቃስ 10:30-35
ኢየሱስ ይህን ታሪክ የተናገረው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ይህን ታሪክ የነገረው ሰው፣ ባልንጀሮቹ አድርጎ የሚመለከተው የእሱ ዓይነት ዘርና ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው። ኢየሱስ ይህ ሰው አንድ አስፈላጊ ቁም ነገር እንዲማር ፈልጎ ነበር፤ ከአይሁዳውያን ወገኖቹ ውጭ ያሉ ሰዎችንም ‘ባልንጀሮቹ’ አድርጎ ሊመለከት እንደሚገባ መገንዘብ ነበረበት። (ሉቃስ 10:36, 37) ይህ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተው አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲማሩበት ተብሎ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ከታሪኩ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
ይህ ታሪክ፣ ጥሩ ባልንጀራ አዘኔታውን በተግባር እንደሚያሳይ ያስተምረናል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ዘር፣ ብሔር ወይም ሌላ ነገር ሳይል ችግር ላይ የወደቀን ሰው ይረዳል። እውነተኛ ባልንጀራ፣ ሌሎች እንዲያደርጉለት የሚፈልገውን ነገር እሱም ያደርጋል።—ማቴዎስ 7:12
ሳምራውያን እነማን ነበሩ?
ሳምራውያን ከይሁዳ በስተ ሰሜን የሚኖሩ ሕዝቦች ነበሩ። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ፣ ቅድመ አያቶቻቸው ከሌሎች ዘሮች ጋር የተጋቡ አይሁዳውያን ነበሩ።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሳምራውያን የራሳቸውን ሃይማኖት አቋቁመው ነበር። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት ቢቀበሉም በአብዛኛው የቀሩትን መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር።
በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን፣ ሳምራውያንን ይንቋቸውና ያገሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:9) እንዲያውም አንዳንድ አይሁዳውያን “ሳምራዊ” የሚለውን ቃል እንደ ስድብ ይጠቀሙበት ነበር።—ዮሐንስ 8:48
“የደጉ ሳምራዊ” ታሪክ እውነተኛ ታሪክ ነው?
የደጉ ሳምራዊ ታሪክ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ይሁን አይሁን መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ አድማጮቹ ነጥቡን በቀላሉ እንዲረዱት ሲል በደንብ የሚያውቋቸውን ልማዶችና ቦታዎች በትምህርቱ ላይ ይጠቅስ ነበር።
ኢየሱስ በተናገረው በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ብዙዎቹ ነገሮች ከታሪክ አንጻር ትክክል ናቸው። የሚከተሉትን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፦
ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚወስደው መንገድ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ነበረው፤ በኢየሩሳሌም እና በኢያሪኮ መካከል ያለው ቁልቁለት በቀጥታ ቢለካ 1 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ታሪኩ ላይ ሰውየው “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ [ወረደ]” መባሉ በእርግጥም ትክክል ነው።—ሉቃስ 10:30
በኢያሪኮ የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ ብዙውን ጊዜ ይህን መንገድ ይጠቀሙ ነበር።
በዚህ ገለል ባለ መንገድ ላይ ብዙውን ጊዜ ወንበዴዎች አድፍጠው በመጠበቅ በመንገደኞች፣ በተለይም ብቻቸውን በሚጓዙ ሰዎች ላይ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር።