በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

አዲስ ቋንቋ መማር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

አዲስ ቋንቋ መማር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

 አዲስ ቋንቋ መማር ራስን መግዛትና ትሕትና ይጠይቃል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚያስቆጭ ነው? በርካታ ወጣቶች ለዚህ ጥያቄ በፍጹም! የሚል መልስ ይሰጣሉ። ይህ ርዕስ እነዚህ ወጣቶች እንዲህ የተሰማቸው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

 ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

 ብዙዎች ይህን የሚያደርጉት ትምህርት ቤት ውስጥ አዲስ ቋንቋ መማር ስለሚጠበቅባቸው ነው። ሌሎች ደግሞ አዲስ ቋንቋ የሚማሩበት የራሳቸው ምክንያት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፦

  •   በአውስትራሊያ የምትኖር አና የተባለች ወጣት የእናቷ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን የላትቪያ ቋንቋ ለመማር ወስናለች። አና እንዲህ ብላለች፦ “ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ላትቪያ ለመሄድ እያሰብን ነው፤ እዚያ የሚኖሩ ዘመዶቼን ሳገኝ ከእነሱ ጋር ማውራት እፈልጋለሁ።”

  •   በዩናይትድ ስቴትስ የተወለደችው ጂና የተባለች የይሖዋ ምሥክር ደግሞ አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ተምራ ወደ ቤሊዝ ሄደች። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ መስማት የተሳነው ሰው መግባባት የሚችለው በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ብቻ ሊሆን ይችላል። መስማት የተሳናቸው ሰዎች የአሜሪካ የምልክት ቋንቋን የተማርኩት መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው ላስተምራቸው ስለፈለኩ መሆኑን ስነግራቸው በጣም ይደነቃሉ!”

 ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት ምሥራች በሁሉም ‘ብሔር፣ ነገድና ቋንቋ’ እንደሚታወጅ ይናገራል። (ራእይ 14:6) በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ አገር ሄደው አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ አዲስ ቋንቋ በመማር ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርገዋል።

 ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት?

 አዲስ ቋንቋ መማር ቀላል አይደለም። ኮሪና የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የሚያስፈልገው አዳዲስ ቃላትን መማር ብቻ እንደሆነ አስቤ ነበር፤ ሆኖም አዲስ ባሕልና አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ መልመድ ጭምር እንደሚጠይቅ ተገነዘብኩ። በእርግጥም አዲስ ቋንቋ መማር ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ነው።”

 አዲስ ቋንቋ መማር ትሕትናም ይጠይቃል። ስፓንኛ የተማረ ጄምስ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በራሳችሁ ላይ መሳቅን መማር አለባችሁ፤ ምክንያቱም ብዙ ስህተት መሥራታችሁ አይቀርም። ግን ይህ የትምህርቱ አንዱ ክፍል ነው።”

 ዋናው ነጥብ፦ ተፈታታኝ ነገሮች ሲያጋጥሟችሁና አልፎ አልፎ ስህተት ስትሠሩ ተስፋ የማትቆርጡ ከሆነ አዲሱን ቋንቋ በተሳካ ሁኔታ የመማር አጋጣሚያችሁ ሰፊ ይሆናል።

 ጠቃሚ ምክር፦ ሌሎች ሰዎች ከአንተ ይልቅ ቋንቋውን በፍጥነት ቢለምዱ በዚህ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብህም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

 ምን ጥቅም ያስገኛል?

 አዲስ ቋንቋ መማር ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ኦሊቪያ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አዲስ ቋንቋ ስትማሩ ከተለያዩ ሰዎች ጋር መተዋወቅና አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ትችላላችሁ።”

 ሜሪ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት አዲስ ቋንቋ መማሯ በራስ የመተማመን ስሜቷን እንዳሳደገላት ተሰምቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ከዚህ በፊት፣ ጠቃሚ ነገር ማከናወን እንደምችል አይሰማኝም ነበር፤ አዲስ ቋንቋ ስማር ግን አንድ አዲስ ቃል ባወቅኩ ቁጥር በጣም ደስ ይለኛል። ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።”

 ከላይ የተጠቀሰችው ጂናም መጽሐፍ ቅዱስን በምልክት ቋንቋ ማስተማር መቻሏ በአገልግሎቷ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን አድርጓታል። እንዲህ ብላለች፦ “መስማት የተሳናቸው ሰዎችን በራሳቸው ቋንቋ ሳነጋግራቸው ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት ማየት በጣም የሚያስደስት ነው!”

 ዋናው ነጥብ፦ አዲስ ቋንቋ መማር አዳዲስ ጓደኞች ለማፍራት፣ በራስ የመተማመን ስሜትህን ለማሳደግና በአገልግሎትህ ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ይረዳሃል። አዲስ ቋንቋ መማር ለሁሉም “ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” ምሥራቹን ማድረስ የምንችልበት ወሳኝ መንገድ ነው።—ራእይ 7:9