በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ከወላጆቼ ጋር ተስማምቼ መኖር የምችለው እንዴት ነው?

ከወላጆቼ ጋር ተስማምቼ መኖር የምችለው እንዴት ነው?

 ጥያቄዎች

  •   ብዙውን ጊዜ የምትጋጨው ከማን ጋር ነው?

    •  ከአባቴ

    •  ከእናቴ

  •   ምን ያህል ጊዜ ትጋጫላችሁ?

    •  ከስንት አንዴ

    •  አልፎ አልፎ

    •  ብዙ ጊዜ

  •   የሚፈጠረው አለመግባባት ምን ደረጃ ላይ ይደርሳል?

    •  ወዲያውኑ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል።

    •  ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ይፈታል።

    •  ብዙ ተጨቃጭቀንም ችግሩ አይፈታም።

 ከወላጆችህ ጋር መግባባት ሲያቅትህ በመካከላችሁ ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እርምጃ መውሰድ ያለባቸው እነሱ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና በዚህ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው በመካከላችሁ የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመቀነስ አንተ ራስህ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። እስቲ በመጀመሪያ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

 ግጭት የሚፈጠረው ለምንድን ነው?

  •   የማመዛዘን ችሎታ። እያደግህ ስትሄድ፣ ልጅ ከነበርክበት ጊዜ ይልቅ ነገሮችን ጥልቀት ባለው መንገድ መመልከት ትጀምራለህ። በተጨማሪም ስለ አንዳንድ ነገሮች ጠንካራ አቋም እያዳበርክ ትሄዳለህ፤ ምናልባትም ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ያለህ አመለካከት ወላጆችህ ካላቸው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “አባትህንና እናትህን አክብር” ይላል።—ዘፀአት 20:12

     የሕይወት እውነታ፦ ግጭት ውስጥ ሳይገቡ ከሌሎች የተለየ አቋም ማራመድ ብስለትና ክህሎት ይጠይቃል።

  •   ነፃነት። ብስለት እያገኘህ ስትሄድ ወላጆችህ የበለጠ ነፃነት ይሰጡህ ይሆናል። ይሁን እንጂ፣ ይህን ነፃነት አንተ በፈለግከው መጠን ወይም በፈለግከው ጊዜ ላይሰጡህ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል።—ኤፌሶን 6:1

     የሕይወት እውነታ፦ ብዙውን ጊዜ ወላጆችህ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡህ የሚያደርገው አሁን የተሰጠህን ነፃነት የምትጠቀምበት መንገድ ነው።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   ከአንተ በሚጠበቀው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ። ለግጭቱ ሙሉ በሙሉ ወላጆችህን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ሰላም ለመፍጠር ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ጄፍሪ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ ግጭት የሚያስነሳው ወላጆች የተናገሩት ነገር ሳይሆን አንተ ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ነው። በእርጋታ መናገር ግጭቱን በማብረድ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18

  •   አዳምጥ። ሳማንታ የተባለች የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆችህ እያዳመጥካቸው እንደሆነ ካስተዋሉ እነሱም እንደሚያዳምጡህ ተገንዝቤያለሁ። እርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ።”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ [ሁኑ]።”—ያዕቆብ 1:19

    ግጭት እንደ እሳት ነው፤ ቁጥጥር ካልተደረገበት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል

  •   ከአንተ ጎን እንደሆኑ አስብ። ችግሩን የምትፈታበት መንገድ ከአንድ ዓይነት ስፖርት ለምሳሌ ከቴኒስ ጨዋታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በዚያኛው ጫፍ ያሉት ወላጆችህ ሳይሆኑ ችግሩ እንደሆነ አድርገህ አስብ። አዳም የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ግጭት ሲፈጠር ወላጆች ለልጃቸው የተሻለ ብለው የሚያስቡትን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ፤ ልጅ ደግሞ ለእሱ የተሻለ እንደሆነ የሚያስበውን ማድረግ ይፈልጋል። በመሆኑም ሁለቱም የተሰለፉት ለተመሳሳይ ዓላማ ነው ሊባል ይችላል።”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሰላም የሚገኝበትን . . . ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19

  •   ወላጆችህን ለመረዳት ሞክር። ሣራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙውን ጊዜ እኛን የሚያሳስቡ ችግሮች እንደሚያጋጥሙን ሁሉ ወላጆችንም የሚያሳስቡ ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው ማስታወሴ ጠቅሞኛል። ካርላ የተባለች ወጣትም ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ራሴን በወላጆቼ ቦታ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። ራሴን እንዲህ እያልኩ እጠይቃለሁ፦ ‘ልጅ እያሳደግኩ ቢሆንና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ምን አደርግ ነበር? ለልጄ የተሻለው ነገር ምንድን ነው?’”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

  •   ታዛዥ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ታዛዥ መሆን እንዳለብህ ይናገራል። (ቆላስይስ 3:20) ታዛዥ ከሆንክ ነገሮች ይበልጥ ይቀሉልሃል። ካረን የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ የሚሉኝን ሳደርግ ውጥረት ይቀንስልኛል። ለእኔ ሲሉ ብዙ መሥዋዕት ከፍለዋል፤ በመሆኑም ቢያንስ ቢያንስ ልታዘዛቸው ይገባል።” ግጭት እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ታዛዥ መሆን ነው!

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል።”—ምሳሌ 26:20

 ጠቃሚ ምክር፦ ከወላጆችህ ጋር ስትነጋገር መግባባት ካቃተህ ማስታወሻ ወይም የስልክ መልእክት በመጻፍ ሐሳብህን ለመግለጽ ሞክር። አሊሲያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሐሳቤን በጥሩ ሁኔታ መግለጽ እንደማልችል ሲሰማኝ ይህን አደርጋለሁ። ይህ ደግሞ በማንም ላይ ሳልጮህ ወይም በኋላ የሚቆጨኝን ነገር ሳልናገር ሐሳቤን እንድገልጽ ረድቶኛል።”