የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያምኑባቸው ነገሮች አንዳንዶቹን የቀየሩት ለምንድን ነው?
ምንጊዜም ቢሆን የምናምንበት ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው፤ በመሆኑም ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር በተያያዘ አዲስ ግንዛቤ ስናገኝ በምናምንበት ነገር ላይ ማስተካከያ እናደርጋለን። a
እንዲህ ያሉት ለውጦች በምሳሌ 4:18 ላይ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፤ ጥቅሱ “የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል” ይላል። የፀሐይዋ ብርሃን እየደመቀ ሲሄድ በአንድ አካባቢ ያሉትን ነገሮች በደንብ ማየት እንደሚቻል ሁሉ አምላክም በቃሉ ውስጥ የሚገኘው እውነት ራሱ በወሰነው ጊዜ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነልን እንዲሄድ አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 1:10-12) መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው አምላክ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ይህን ሂደት አፋጥኖታል።—ዳንኤል 12:4
ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ መደረጉ ሊያስገርመንም ሆነ ሊረብሸን አይገባም። ጥንት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮችም የተሳሳተ ግንዛቤ የነበራቸው በመሆኑ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓቸዋል።
ሙሴ ራሱን የእስራኤል ብሔር ነፃ አውጪ አድርጎ ያቀረበው አምላክ ካሰበው ጊዜ 40 ዓመት ቀደም ብሎ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 7:23-25, 30, 35
ሐዋርያቱ ስለ መሲሑ ሞትና ትንሣኤ የተነገረውን ትንቢት አልተረዱትም ነበር።—ኢሳይያስ 53:8-12፤ ማቴዎስ 16:21-23
ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ‘የይሖዋን ቀን’ በተመለከተ የተሳሳተ ግንዛቤ ነበራቸው።—2 ተሰሎንቄ 2:1, 2
ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ የጥንት አገልጋዮቹ የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል፤ እኛንም በተመሳሳይ መንገድ እንዲረዳን እንጸልያለን።—ያዕቆብ 1:5
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን በተመለከተ በነበረን ግንዛቤ ላይ ያደረግናቸውን ለውጦች ለመደበቅ አንሞክርም። እንዲያውም እነዚህን ማስተካከያዎች በጽሑፎቻችን ላይ እናወጣለን። ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ላይ “ስለምናምንባቸው ነገሮች ያገኘነው አዲስ ግንዛቤ” ብለህ ፈልግ።