በቬኔዙዌላ በአስቸጋሪ ጊዜ ይሖዋን ማገልገል
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቬኔዙዌላ ከባድ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ገጥሟታል። ኤድጋር የተባለ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኑሮው ሁኔታ በጣም ነው ያሽቆለቆለው። የትም ሳንሄድ፣ ወደ ሌላ አገር የተሰደድን ያህል ነው የተሰማን!”
ታዲያ ኤድጋር ይህን ሁኔታ እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ካርመን የኑሮ ደረጃው ዝቅተኛ ወደሆነባቸው አገሮች ሄደው መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን እንኳ ሳያገኙ ስለሚኖሩ ሚስዮናውያን አሰብን። ይህም አኗኗራችንን ቀለል ለማድረግና አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር አነሳሳን፤ ለምሳሌ የጓሮ አትክልት ተከልን።”
ኤድጋርና ካርመን ሌላም ያደረጉት ነገር አለ። በጭንቀት የተዋጡትን ጨምሮ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማጽናናት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። (1 ተሰሎንቄ 5:11) ኤድጋር እንዲህ ብሏል፦ “እነሱን ከማጽናናት ባለፈ፣ ችግር ላይ ያሉ ሌሎችን በመርዳት የሚገኘውን ደስታም እንዲቀምሱ አበረታታናቸው።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
የአገልግሎት ጥረታቸው ተባርኳል
ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጀመረበት ወቅት አርሄኒዝ ለዘመዶቹ ለመመሥከር ወሰነ። አንዳንዶቹ በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ።
አርሄኒዝ የኢንተርኔት አገልግሎት የማያገኙ ዘመዶቹ የ2020ን የክልል ስብሰባ እንዲካፈሉ ፈልጎ ነበር። በአቅራቢያቸው ባለ ከተማ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር የተቀዳውን ፕሮግራም ሰጣቸው። የአርሄኒዝ ዘመዶች ደግሞ ትልቅ ስክሪን ያለው ቴሌቪዥንና ድምፅ ማጉያዎች ተዋሱ። አርሄኒዝ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ስልክ ደወለላቸውና አብሯቸው ጸለየ። እንዲህ ያለ ጥረት በማድረጉ 4 ዘመዶቹና ሌሎች 15 ሰዎች ፕሮግራሙን መከታተል ችለዋል።
እምነትና ፍቅር ለተግባር አነሳስቷቸዋል
ሃይሮ እና ጆኣና የተባሉ ባልና ሚስት ያደረጉትን እንመልከት፤ በጉባኤያቸው ውስጥ መኪና ያላቸው እነሱ ብቻ ናቸው። እነዚህ ባልና ሚስት መኪናቸውን ሌሎችን ለመርዳት ይጠቀሙበታል። ችግሩ ግን ነዳጅ ማግኘት ቀላል አለመሆኑ ነው። ሃይሮ “ነዳጅ ለማግኘት ለሰዓታት አንዳንዴም ሌሊቱን ሙሉ መሰለፍ ያስፈልገናል” ብሏል።
ሃይሮ ያደረጉት ጥረት የሚያስቆጭ እንዳልሆነ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ለወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ስናደርስላቸው ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆኑ ማየት ያስደስተናል፤ ወንድሞቻችን እኛን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚያሟላውን ይሖዋን ያመሰግናሉ።”—2 ቆሮንቶስ 9:11, 14
ሁሉም ሰው እርዳታ ማበርከት ይችላል
የኖሪአኒን ምሳሌ እንመልከት፤ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ቢሆንም ሌሎችን ለመርዳት ስታስብ እንደ ልጅ ተደርጋ እንዳትቆጠር ትፈራ ነበር። ከዚያ ግን በ1 ጢሞቴዎስ 4:12 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበበች፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት . . . አርዓያ ሁን።”
ይህ ጥቅስ ኖሪአኒ በጉባኤያቸው የሚገኙ አረጋውያንን እንድትረዳ አነሳሳት፤ በደብዳቤ ምሥክርነት እንዲሳተፉ ትረዳቸው አልፎ ተርፎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ትጋብዛቸው ጀመር። በተጨማሪም ስልክ ትደውልላቸው እንዲሁም የሚያጽናኑ የጽሑፍ መልእክቶችን ትልክላቸው ነበር። ኖሪአኒ “ይሖዋ ብዙ ነገር ማከናወን እንደምችል አስተምሮኛል” ብላለች።
በቬኔዙዌላ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ያም ቢሆን በአገልግሎት በቅንዓት መካፈላቸውንና አንዳቸው ለሌላው “የብርታት ምንጭ” መሆናቸውን ቀጥለዋል።—ቆላስይስ 4:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2