የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙት እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት፣ ስብሰባ ለማድረግ የሚጠቀሙባቸውን ቦታዎች ንድፍ አውጥተው ሲገነቡ ቆይተዋል። እነዚህ የአምልኮ ቦታዎቻቸው ‘የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾች’ ተብለው ይጠራሉ። በአካባቢያችሁ እንዲህ ያሉ አዳራሾች ተገንብተዋል? እነዚህ አዳራሾች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙትስ እንዴት ነው?
“ማኅበረሰቡን የሚያስደስቱ ስጦታዎች”
የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾችን ማራኪ በሆነ መንገድ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የስብሰባ አዳራሾችን ግንባታ በማስተባበር ሥራ የሚሳተፈው ጄሰን “ዓላማችን፣ የምንገነባው እያንዳንዱ የስብሰባ አዳራሽ በአካባቢው ከሚገኙ በጣም ማራኪና ውብ የሆኑ ሕንፃዎች መካከል እንዲመደብ ነው” ሲል ተናግሯል። የሥነ ሕንፃ ባለሙያ የሆነና የስብሰባ አዳራሾች ንድፍ ከሚያወጣው ቡድን ጋር የሚሠራ አንድ የይሖዋ ምሥክርም እንዲህ ብሏል፦ “የስብሰባ አዳራሾቻችን ተገንብተው ሲጠናቀቁ ማኅበረሰቡን የሚያስደስቱ ስጦታዎች እንዲሆኑ እንዲሁም አካባቢው ማራኪ ገጽታ እንዲላበስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንዲሆኑ እንፈልጋለን።”
የስብሰባ አዳራሾቹን በመገንባቱ ሥራ የሚካፈሉት፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ሕንፃዎችን ለመገንባት ከልባቸው የሚፈልጉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። የእነዚህ ሠራተኞች ግሩም ችሎታ የሌሎችን ትኩረት ብዙውን ጊዜ ይስባል። ለምሳሌ ቴክሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባለችው በሪችመንድ ከተማ በቅርቡ የተካሄደውን ግንባታ የተመለከተ አንድ የአካባቢው ሕንፃ ተቆጣጣሪ የስብሰባ አዳራሹ ጣሪያዎች የተሠሩበት መንገድ ከዚያ በፊት ከተመለከታቸው ሁሉ የላቀ እንደሆነ ተናግሯል። ጃማይካ ውስጥ በሚገኝ አንድ ደሴት ደግሞ አንድ የሕንፃ ተቆጣጣሪ አዳዲስ የሕንፃ ተቆጣጣሪዎች የሚገኙበት ቡድን የስብሰባ አዳራሻችንን ግንባታ እንዲጎበኝ አድርጎ ነበር፤ ከዚያም እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ስለ እነዚህ ሰዎች ጨርሶ ሐሳብ አይግባችሁ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚሠሩት ንድፉን ተከትለው ነው፤ እንዲያውም ሕንፃዎቻቸው በአካባቢያችን ለሕንፃዎች የወጣውን ደረጃ አልፈው ሄደዋል።” በፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የሕንፃ ተቆጣጣሪም እንዲህ ብሏል፦ “ሆስፒታሎችንና ትላልቅ የመንግሥት ግንባታዎችን ስቆጣጠር ቆይቻለሁ፤ እንደዚህ የተደራጀ አሠራር ግን አይቼ አላውቅም። በጣም ጥሩ ሥራ እያከናወናችሁ ነው።”
ጎረቤቶቻችንን ይጠቅማሉ
በስብሰባ አዳራሾቻችን የሚደረጉት ስብሰባዎች በዚያ የሚገኙትን ሰዎች በእጅጉ ይጠቅማሉ። ተሰብሳቢዎቹ የተሻለ አባት፣ እናት እንዲሁም ልጅ ለመሆን የሚረዳቸውን ትምህርት ያገኛሉ። የስብሰባ አዳራሾቹን ንድፍ ከሚያወጣው ቡድን ጋር የሚሠራው ሮድ እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ የስብሰባ አዳራሽ፣ ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን መከተልን የሚያበረታታ የትምህርት ማዕከል ነው፤ ይህም ለመላው ማኅበረሰብ ጥቅም ያስገኛል። በሕይወት ውስጥ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙህ በእነዚህ ቦታዎች እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ማጽናኛ እና መንፈሳዊ እርዳታ የሚፈልጉ ሁሉ ወደ ስብሰባ አዳራሾቹ ሲሄዱ ግሩም አቀባበል ይደረግላቸዋል፤ ደግሞም ብዙ ጥቅም ያገኛሉ።”
በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የሚሰበሰቡት ሁሉ ስለ ጎረቤቶቻቸው በጥልቅ ያስባሉ፤ በአካባቢው አደጋ ሲደርስ ደግሞ ፈጣን እርዳታ ይሰጣሉ። ለምሳሌ፣ በ2016 ማቲው የተባለ ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የባሃማስ ደሴቶችን በመታበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳት የደረሰባቸውን 254 ቤቶችን ጠግነዋል። ቤታቸው በጎርፍ ተጥለቅልቆባቸው የነበሩ ቫይለት የተባሉ አንዲት የሰማንያ ዓመት ሴት፣ በቡድን ሆነው የእርዳታ ሥራ እያከናወኑ ወደነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሄዱ። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮቹ የቻሉትን ያህል ከረዷቸው ገንዘብ ሊከፍሏቸው ፈቃደኛ እንደሆኑ ተናገሩ። የይሖዋ ምሥክሮቹ ግን ምንም ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ያም ቢሆን የቫይለት ጣሪያ ማፍሰሱን እንዲያቆም ሲሉ ጣሪያቸውን አደሱላቸው። ከዚያም የሳሎናቸውን ኮርኒስ ቀየሩላቸው። በዚህ የተነሳ ቫይለት ሁሉንም የቡድኑን አባላት እያቀፉ በተደጋጋሚ አመሰገኗቸው፤ በተጨማሪም “በእርግጥም እናንተ የአምላክ አገልጋዮች ናችሁ!” ብለዋቸዋል።
‘የስብሰባ አዳራሹ በእኛ አካባቢ መገንባቱ ያስደስተናል’
የስብሰባ አዳራሾቹ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ ሲባል በአዳራሾቹ በሚሰበሰቡት ጉባኤዎች ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ለአዳራሹ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ይህም ግሩም ውጤቶች አስገኝቷል። ለምሳሌ፣ በአሪዞና፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለ አንድ ትንሽ ማኅበረሰብ ውስጥ የምትኖር አንዲት ሴት በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ተጋብዛ ነበር። ይህች ሴት አዳራሹ በጣም በጥሩ መንገድ እንደተያዘ ተናግራለች፤ እንዲህ ያለውን ጥሩ ሁኔታ ላይ ያለ አዳራሽ ለማደስ እና ለማሻሻል ዕቅድ እንደተያዘ መስማቷ ደግሞ የበለጠ አስገርሟታል። ሴትየዋ በከተማው ለሚታተም ጋዜጣ ትጽፋለች፤ በኋላም የስብሰባ አዳራሹ በጥሩ መንገድ እንደተያዘ የጻፈችው ዘገባ በጋዜጣው ላይ ወጥቷል። ዘገባው ሲደመድም “የስብሰባ አዳራሹ . . . በእኛ አካባቢ መገንባቱ ያስደስተናል” ይላል።
በመላው ዓለም የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾች ይገኛሉ። አንተም መሰብሰቢያ ቦታችንን መጥተህ እንድትጎበኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። በዚያም ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግልህ መተማመን ትችላለህ።